በዚህ ዓመት ከ150 በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ተዘጋጅተዋል

121

ሚያዝያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በዚህ ዓመት ከ150 በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የተዘጋጁ መሆኑን የአዲስ አበባ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ ንዑስ ዘርፍ የተደራጁና ለ11ኛ ጊዜ የሚመረቁ የማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግና ማምረቻ ኢንዱስትሪን ጎብኝተዋል።

የአዲስ አበባ የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኢንተርፕራይዝ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍስሐ ጥበቡ፤ የጉብኝቱ ዓላማ ኢንተርፕራይዞቹ በሽግግሩ ስኬታማ ሆነው አንዲሰሩ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በዘንድሮው ዓመት መስፈርቱን ያሟሉ ከ150 በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከሚሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች መካከል በቆዳ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በብረታ ብረትና በእንጨት ስራዎች የተደራጁ ከ80 በላይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተደራጁ ናቸው።

በጉብኝቱ የመካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ምን እንደሚያስፈልጋቸው ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑ ተገልጿል።

የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ በማከል እንዲሰሩና ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዲያዩ ጉብኝቱ እንደተዘጋጀም ኃላፊው ተናግረዋል።

አብዛኛዎቹ ኢንተርፕራይዞች ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገር የሚያስችላቸው ሥራዎች ውስጥ እየገቡ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በ50 ሺህ ብር ካፒታል ተነስተው እስከ መካከለኛ የደረሱ 1 ሺህ 458 ኢንተርፕራይዞች በ10 ዙር መመረቃቸው ታውቋል።

መካከለኛ ኢንዱስትሪ የሚባሉት ሠራተኛ ቀጥረው ማሰራት የቻሉና ወደ ሰፊ ምርት ውስጥ የገቡ የካፒታል አቅማቸው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ መሆኑን  ኃላፊው አስረድተዋል።

በዚህ ዓመት ለ11ኛ ጊዜ 179 በብረታ ብረትና የእንጨት ሥራ፣ በኮንስትራክሽንና በጨርቃ ጨርቅ ስራ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችን እንደሚያስመርቅ ታውቋል።

ተመራቂዎቹ የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንጂነሪንግና ማምረቻ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሰንሻይንና ኖህ ሪል ስቴትን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም