በሰሜን ወሎ ዞን በመስኖ ከለማ መሬት ከአምናው በ471 ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ተገኘ

120

ወልዲያ፣ ሚያዝያ 29/2014 ዓ.ም. ( ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን በዘንድሮው የበጋ ወራት በመጀመሪያው ዙር በመሰኖ ከለማው መሬት ከአምናው በ471 ሺህ ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መገኘቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ቦጋለ ስጤ ለኢዜአ እንገለጹት አካባቢው አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ የጦርነት ቀጠና ሆኖ ቆይቶ ነበር።

በሀገር መከላከያ ሠራዊትና በፀጥታ ኃይሎች አካባቢው ከጦርነት ቀጠና በመውጣቱና በሽብር ቡድኑ የቀነሰውን የመኸር ሰብል ምርት በመስኖ ለማካካስ  የተቀናጀ ጥረት መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር የውሃ ሀብትን በመጠቀም በመጀመሪያው ዙር መሰኖ ልማት 13ሺህ 770 ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብልና አትክልት ማልማት ተችሏል ብለዋል።

በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ከ15 ሺህ 200 በላይ ሄክታር መሬት ለማልማት የታቀደ ቢሆንም በሽብር ቡድኑ ወራራ ምክንያት የተሳካው የዕቅዱ 90 በመቶ ያህል እንደሆነም አስረድተዋል።

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ ከመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የተገኘ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ471 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው።

የመስኖ ልማቱ ውጤታማ እንዲሆን ከ9 ሺህ ኩንታል በላይ ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፤  አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ ተጠቅሟልም ብለዋል።

በመስኖ ልማቱ 89ሺህ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ የተለያየ አትክልት መልማቱን ምክትል ኃላፊው ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁለተኛ ዙር የመስኖ ልማት 8 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በጤፍ፣ በርበሬ፣ በቲማቲምና በሽንኩርት መልማቱን ጠቅሰው በልማቱ 37ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

በራያ ቆቦ ወረዳ ከ07 ቀበሌ አርሶ አደርሶ አደሮች አቶ ምስጋን ደሳለ እንዳሉት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ልማት 200 ኩንታል የሽንኩርት ምርት ሊያስገኝ የሚችለውን ቡቃያ በሽብር ቡድኑ ወድሟል።

የአካባቢው ሰላም አሁን በመመለሱ በሁለተኛ ዙር መስኖ 80 ኩንታል ምርት ሊያስገኝ የሚያስችል በርበሬ፣ ጤፍ፣ ስንዴና ቲማቲም እያለሙ ሲሆን፤ ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት 232 ሺህ ብር የሚገመት የሽንኩርትና ቲማቲም ምርት እንደወደመባቸው የራያ ቆቦ ወረዳ የአራዶም ቀበሌ አርሶ አደር አታሎ ገልጸዋል።

በዚህ ቁጭት በመነሳት በሁለተኛ ዙር አንድ ሄክታር ተኩል መሬት በቆላ ስንዴና ቲማቲም እያለሙ ሲሆን፤ የተሻለ ምርትም እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም