የመከባበር፣ የፍቅርና የሰላም እሴቶች በማስቀጠል ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቃለን- የ”አሆላሌ” ፌስቲቫል ተሳታፊዎች

87

ደሴ ፤ ሚያዝያ 29/2014(ኢዜአ) ከአባቶቻችን የወረስነውን የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የፍቅርና የሰላም እሴቶችን በማስቀጠል ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቃለን ሲሉ የ”አሆላሌ” ፌስቲቫል ተሳታፊዎች ተናገሩ።

“ባህላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን” በሚል መሪ ሀሳብ  በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ የ”አሆላሌ” ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው።

“አሆላሌ”በደቡብ ወሎ   በልጃገረዶችና ጎረምሶች የሚከወን ባህላዊ ጨዋታና የአብሮነት መገለጫ ሲሆን፤ ከፌስቲቫሉ  ተሳታፊዎች መካከል ወጣት አሚናት አህመድ አንዷ ናት።

ወጣቷ እንደገለጸችው፤  ከታላላቆች የተወረሱ  ለአንድነትና ሰላም መስፈን የጎላ ፋይዳ ያላቸው በርካታ ባህልና እሴቶች አሉ።

በተለይ ከአባትና እናቶቻችን የወረስነውን የአብሮነት፣ የመከባበር፣ የሰላምና የፍቅር ባህልና እሴት አስቀጥለን ኢትዮጵያን በጋራ እንጠብቃለን ብላለች።

እንደ ”የአሆላሌ” ዓይነት ባህላዊ ጨዋታዎችንና ክዋኔዎችንም በአደባባይ በማክበር ባህልና ታሪካችንን እናስቀጥላለን ብላለች ወጣት አሚናት።

ወጣት እንድሪስ ማሩ በበኩሉ፤ ከአባቶቻችን የወረስናቸውን ባህላዊ እሴቶች ጠብቀን በአንድነት የኢትዮጵያን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ ዝግጁ ነን ሲል ገልጿል።

የ”አሆላሌ” መተጫጫችን፣ መደሰቻችንና አንድነታችንን የምናጠናክርበት ባህላዊ ጨዋታችን ነው ብሏል።

የ”አሆላሌ” ባህል አምባሳደር አርቲስት ሀናን አብዱ ፤ ባህልና ወግን ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ በኪነ ጥበብ አዋህዶ የገቢ ምንጭ ማድረግ እንደሚገባ ተናግራለች።

“የአሆላሌ”ን በተለያዩ ዘፈኖችና የኪነ-ጥበብ ስራዎች አካቶ ለዓለም በማስተዋወቅም የድርሻዬን እወጣለሁ” ብላለች።

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን መኮንን እንዳሉት፤ “አሆላሌ”በደቡብ ወሎ  በልጃገረዶችና በጎረምሶች የሚካሄድ የጨዋታ፣  የመተጫጫ፣ የመደሰቻና የአብሮነት መገለጫ  ባህላዊ ክዋኔ ነው፡፡

አባቶችና ሽማግሌዎችም ይመርቁበታል ብለዋል፡፡

ባህላዊ አመጣጡንና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በአደባባይ እየተከበረ ለትውልድ እንዲተላለፍ፣ አብሮነትና ሰላም ማጎልበቻ እንዲሆንም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራን ሲሉ ገልጸዋል።

፤ በክልሉ ያሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ክዋኔዎችን፣ ቅርስና ትውፊቶችን በመጠቀበቅ  የቱሪዝም ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ናቸው።

ትውልዱ በህዝቡ ዘንድ ተጠብቀው የቆዩ ዘመን ተሻጋሪ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች በማጎልበት ለሀገሪቱ  ዘላቂ ሰላም መጠበቅ ሊጠቀምበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

“አሆላሌ”  ልክ እንደነ ሶለል፣ አሸንድዬና አገው ፈረሰኞች በድምቀት በማክበር የኢትዮጵያና የአለም ህዝብ እንዲያውቀው ይደረጋልም ብለዋል።

በፌስቲቫሉ ላይ ጭፈራና ሎሚ ውርወራን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች እየተካሄዱ ሲሆን በሥርዓት ላይ  የክልል፣ የዞንና የወረዳ እንዲሁም   የወሎ ዩኒቨርስቲ አመራሮች፣የሀገር ሽማግሌዎችና ባለድርሻ አካላት መታደማቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።