በህገ ወጥ መልኩ በመደራጀት በህዝብ ላይ እንግልትና ዘረፋ በሚፈፅሙ ጫኝና አውራጆች ላይ ፖሊስ እርምጃ ይወስዳል

170

ሚያዚያ 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህገ ወጥ መልኩ በመደራጀት በህዝብ ላይ እንግልትና ዘረፋ በሚፈፅሙ ጫኝና አውራጆች ላይ የተጠናከረ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የመዲናዋ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በህጋዊ መንገድ በጫኝና አውራጅነት ከተደራጁ ወጣቶች ጋር እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

የፖሊስ ኮሚሽኑ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን፤ በጫኝና አውራጅ ስራ ዙሪያ በአዲስ አበባ ያሉ ችግሮችን የሚያመላክት ጹሁፍ አቅርበዋል።  

በመዲናዋ በህገ ወጥ መልኩ በመሰባሰብ በህዝብ ላይ እንግልትና ዘረፋ እየፈፀሙ ያሉ ህገ ወጥ ጫኝና አውራጆች ስለመበራከታቸው ጠቅሰዋል።

በዚህም "ባለንብረቶች እቃው ከተገዛበት በላይ የተጋነነ ዋጋ እየተጠየቁ ነው" ያሉት ኮማንደሩ ለማህበረሰቡ እና ለከተማው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆናቸውን አብራርተዋል።

በእነዚህ ህገ ወጦች የንብረት መሰረቅ፣ ጉዳት መድረስና ሌሎችም ተጓዳኝ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በእንደዚህ ዓይነት ህገ ወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ላይ ፖሊስ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አሳስበዋል።

የአደራጅ አካላት የቁጥጥር መላላት እና በዚህ ጉዳይ ህብረተሰቡ ለጸጥታ አካላት ጥቆማ አለመስጠቱ ለወንጀሉ መበራከት ምክንያት መሆኑን ኮማንደር ሰለሞን ገልጸዋል።

በአንዳንድ ህግ አስከባሪዎች በኩልም ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ማስተካከያ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም የችግሩን አሳሳቢነት አንስተው በቀጣይ መፍትሄ እንደሚያሻው አመላክተዋል።

የችግሮቹ መነሻ በአብዛኛው በህገ ወጥ መንገድ በተደራጁት ጫኝና አውራጆች በመሆኑ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጥበትና ህጋዊ መስመር ሊያስይዛቸው ይገባል ብለዋል።

በጫኝና አውራጅነት ተደራጅተው በመልካም አርአያነታቸው የሚጠቀሱ በመኖራቸው ተሞክሯቸው ለሌሎች እንዲደረስ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም