የምግብ ዋስትና ችግሮችን ለመፍታት ህብረተሰቡ በግብርናና ሌሎች ልማቶች ላይ መረባረብ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ

125

ዲላ ፤ ሚያዝያ 29/2014(ኢዜአ) የምግብ ዋስትና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ በግብርናና ሌሎች ልማቶች ላይ በነቂስ ወጥቶ መረባረብ እንደሚጠበቅበት ተገለጸ።

በሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ ውይይቱ ሲጀመር እንዳሉት፤ በልማትና ሰላም ግንባታ ላይ የዜጎች ቀጥተኛ ተሳትፎ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ ነው።

ጥቂቶች በሚፈጥሩት የሰላም ችግር በርካቶች ተጎጅ መሆናቸውን አንስተው፤ ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ለሰላም ግንባታ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ የምግብ ዋስትና ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት  በግብርናና ሌሎችም የልማት ስራዎች ላይ በነቂስ ወጥቶ መረባረብ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትንና ስራ አጥነት ለማቃለል  የሚደረገውን ጥረትም ማገዝ እንዳለበት ጠቁመዋል።

የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ፤ በውይይቱ መድረክ  ሀገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰነድ አቅርበው ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የመንግስት አመራሮች፣ የሃይማኖት  መሪዎች፣ የባህልና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሴቶችና ወጣት አደረጃጀት ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከዲላ ዘግቧል።