ዘመን ተሻጋሪ የመቻቻልና የአንድነት ባህልና እሴት በአግባቡ ተጠቅመን የሃገራችንን ሰላም መጠበቅ ይገባናል

191


ሚያዝያ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ)"ባህላችን ለሰላማችንና ለአንድነታችን! "በሚል መሪ ሀሳብ "የአሆላሌ" ፌስቲቫል አካል የሆነ የፓናል ውይይት ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሂዷል፡፡


''አሆላሌ''በደቡብ ወሎ ዞን በልጃገረዶችና በጎረምሶች የሚከወን ባህላዊ ጨዋታና የመተጫጫ፣የመደሰቻና የአብሮነት መገለጫ ባህላዊ ክዋኔ ነው፡፡


በተለያዩ በዓላት ደግሞ የባህል ልብስ ተለብሶ በይበልጥ በጭፈራ፤ በባህል እስክታና ሎጋ የሚካሄድ ባህላዊ ክዋኔ ሲሆን አባቶችና ሽማግሌዎችም ይመርቁበታል፡፡


ወጣት ወንዶች በትግል፣በዱላ ምከታ፣በእጅ ንጥቂያና በሆታ ጀግንነታቸውን ለልጃገረዶች የሚያሳዩበት በአል መሆኑን ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያሳያል።


''አሆላሌ'' ባህልና እሴቶችን ያካትታል፤ ለምሳሌ አበጋር፤ ሽምግልና፤ ፋጡማ ቆሬ ይጠቀሳሉ።


የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ከፍተኛ የትምህርት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን አስተባባሪና የባህል፣ እሴትና ማህበራዊ ፋይዳ ተመራማሪ ዶክተር ከበደ ካሣ ለኢዜአ እንደገለጹት በትውልዶች መካከል ሲሸጋገር የቆየውን መልካም ባህል ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል።


ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገሮች የሚተርፍ ድንቅ ቱባ ባህልና እሴት ያላት ታላቅ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ "የሽምግልና፣ የአበጋር፣ የገዳና ሌሎች ስርዓቶችን ተጠቅመን አለመግባባቶችን መፍታት አለብን" ብለዋል፡፡


''በተለይ አሁን እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በባህላችን መሰረት ተነጋግረን በመፍታት አንድነታችንና ሰላማችንን ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ የለንም፤ ትውልዱም አባቶችን ማዳመጥና ባህሎችን ማስቀጠል ይኖርበታል'' ሲሉም ተናግረዋል።


በሐሰት ትርክት አንዱን የበላይ ሌላው የበታች በማድረግ ለጠላት በር መክፈት ሳይሆን አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት አክብሮና ተከባብሮ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን በጋራ መጠበቅ የግድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


''በህዝቡ ዘንድ ተጠብቀው የቆዩ ዘመን ተሻጋሪ የመቻቻልና የአንድነት እሴቶች በማጎልበት የሃገራችን ዘላቂ ሰላም መጠበቅ ይገባናል'' ሲሉም ተናግረዋል።


የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮንን በበኩላቸው "የወሎን አብሮነት፣ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት ለትውልድ ለማስተላለፍ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሰራ ነው" ብለዋል፡፡


''ያለንን ድንቅ ባህል አስቀጥለን፣ ለችግሮቻችንም በባህልና እሴቶቻችን መሰረት መፍትሄ እየሰጠን አንድነታችንና ሰላማችንን በጋራ በማስጠበቅ የብልጽግና ጉዟችንን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል'' ብለዋል፡፡


በፓናል ውይይት የተጀመረው "የአሆላሌ" ፌስቲቫልም "የአሆላሌ" ከደሴ እስከ ሐይቅ ዳርቻ በሚል መርህ በተሰናዱ ዝግጅቶች በሁለቱ ከተሞች እንደሚከበር አመላክተዋል፡፡


"የአሆላሌ" በልጃገረዶችና ጎረምሳ ወንዶች ክብረ በዓላትን ለማድመቅ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ "በአረፋ፣ በአሹራ፣ በገና፣ በጥምቀት፣ በአስተርዮ ማርያምና በጥር ሚካኤል በዓላት ላይ በስፋት ይከወናል" ብለዋል፡፡


የአምባሰል ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አረጉ ይማም በሰጡት አስተያት ''የአሆላሌ''ን በጋራ እያከበሩ አንድነትንና ሰላምን ከመጠበቅ ባለፈ፤ በባህላዊ ክዋኔው በመተጫጨት ትዳርም ይመሰረታል፡፡


በደቡብ ወሎ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ባዘጋጁት ፌስቲቫል ላይ አመራሮች፣ምሁራን፣ አርቲስቶችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም