በምዕራብ ጎንደር ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች 9ሺህ ሄክታር ያህል መሬት ተዘጋጅቷል

103

መተማ ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ)... በምዕራብ ጎንደር ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ወደ 9ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት መዘጋጀቱን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 97 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱ ተገልጿል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መሰንበት መልካሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የአካባቢውን የግብርና ኢንቨስትመንት ለማነቃቃት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በተለይ አካባቢው ለሰሊጥ፣ ለአኩሪ አተርና ሌሎች ለውጭ ገበያ ለሚቀርቡ ምርቶች ምቹ በመሆኑ ዕድሉን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

በዞኑ በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ወደ 9ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት መዘጋጀቱን ጠቅሰው መሬቱን በህጋዊ ጨረታ ለአልሚ ባለሃብቶች እንዲሚተላለፍ ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በከተሞች በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ባለሃብቶች ደግሞ 200 ሄክታር መሬት  ተዘጋጅቷል።

በዚህ ዓመት ግብርናን ጨምሮ በሌሎች የልማት ዘርፎች ለመሰማራት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው ጥያቄ ላቀረቡ  97 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት መካከል 53 ባለሃብቶች በግብርናው የሚሰማሩ ሲሆን፤ ህጋዊ አሰራርን ተከትሎ እንደሚስተናገዱ አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ ባለሃብቶች 17 በአምራች ኢንዱስትሪ፣ 26 በአገልግሎት እና አንድ ባለሃብት ደግሞ በኮንስትራክሽን ዘርፎች ለመሰማራት ያቀዱ ናቸው ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብቶች በሙሉ አቅም ወደ ስራ ሲገቡ ከ34 ሺህ በላይ ለሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በዞኑ ቀደም ሲል የእርሻ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ወሰደው ወደ ተግባር የገቡ 858 ባለሃብቶች ከ90 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ላይ ናቸው።

በገንዳ ውሃ ከተማ በሰሊጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት 200 ሚሊዮን ብር ካፒታል አስመዝግበው ፈቃድ የወሰዱት አቶ ንጉሴ ካሳው እንዳሉት ወደ ግንባታ ለመግባት የቦታ ፈቃድ ጠይቀው እየጠበቁ ነው።

ባለሃብቱ አክለውም በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ ሲገቡ ከ100 ለሚበልጡ ወገኖች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ምርቶችን ለማምረት እንደሚፈልጉ የገለጹት ደግሞ በእርሻ ኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት ባለሃብት አቶ ተመስገን ደሴ ናቸው።

ባለሃብቱ 100 ሄክታር መሬት ለማልማት መወሰናቸውን ገልጸው ክልሉ የሚያወጣውን ጨረታ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው በግንባታ ሂደት፣ በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም