ከ10 ሺህ በላይ ተማሪዎች ''አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ'' የቃልኪዳን ፕሮጀክት ተጠቃሚ ሆነዋል- ጎንደር ዩኒቨርሲቲ

169

ጎንደር ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ''አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ'' በሚለው የቃል ኪዳን ቤተሰብ ፕሮጀክቱ ከ10 ሺ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በመጭው ሳምንት የሚቀበላቸውን ከ5ሺ በላይ አዲስ ተማሪዎች በቤተሰብ ፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን አመልክቷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር  አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንደገለጹት ከተጀመረ 3ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የቤተሰብ ፕሮጀክቱ ተማሪዎችን በኢትዮጵያዊ አንድነት ማስተሳሰር ዓላማ ያለው ነው፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ከ10 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎች እያንዳንዳቸው በከተማው እንደ ወላጅና አሳዳጊ የሚንከባከቧቸውን ቤተሰብ ማፍራት እንዲችሉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎች የጎንደርና አካባቢውን ማህብረሰብ የባህል፣እምነትና እሴቶችን አውቀው ከማህብረሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲፈጥሩ ያስቻለ መሆኑን ገልፀዋል።

ተማሪዎቹ በመሰረቷቸው ቤተሰባዊ ግንኙነት መሰረት በበዓል ወቅት አብሮ የማሳለፍ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲያጋጥማቸውም እንደ ወላጅና ልጅ በቅርብ እየተገናኙ በመመካከር በጋራ የመፍታት ባህላዊ እሴቶች ማዳበራቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው የቤተሰብ ፕሮጀክቱን የሚከታተልና የሚያስፈጽም በጽህፈት ቤት ደረጃ አዋቅሮ ባለፉት ሁለት አመታት ፕሮጀክቱን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ግንቦት 1 ቀን  2014 ዓም 5 ሺ 337 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል የእንኳ ደህና መጣችሁ ስነ ስርአት  ለማድረግ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

አዲስ የሚገቡ ተማሪዎችን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመው ቤተሰባዊ ትስስሩን ለመፍጠር የሚሹ ፈቃደኛ የሆኑ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችን የመመዝገብ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በቤተሰብ ፕሮጀክቱ አንድ ተማሪ ተቀብለው እንደ ወላጅ በመንከባከብ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  በጎንደር ከተማ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ቻላቸው መኮንን ናቸው፡፡

''ዩኒቨርሲቲው እንደ ወላጅ እንድንከባከበው የሰጠኝን ተማሪ ለእረፍት ቤተሰቡ ጋ ቆይቶ ሲመጣ እንደ ልጅ እንኳን ደህና መጣህ በማለት እቀበለዋለሁ፤ ለእረፍት ሲሄድም የትራንስፖርት ውጭውን እሸፍንለታለሁ'' ያሉት ደግሞ  የከተማው ነዋሪ አቶ አበጀህ ተሰማ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ ወጣት መሳይ ኢርጴሳ በበኩሉ ''የቤተሰብ ፕሮጀክቱ እንደ ወላጅ የሚንከባከቡኝ ጥሩ ቤተሰብ አስገኝቶልኛል'' ብሏል፡፡

''በዓልን በጋራ አብሬ አሳልፋለሁ፤ በየሳምንቱም እንጠያየቃለን ፤ትምህርቴንም ያለአንዳች ስጋትና ብቸኝነት ሳይሰማኝ ለመከታታል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮልኛል'' ሲል ተናግሯል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመደበኛና ተከታታይ መርሃ ግብር ከ40  ሺህ በላይ ተማሪዎች ተቀብሎ በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም