መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የመልማት አቋም በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ማገዝ አለባቸው

97

ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የመልማት አቋም በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ማገዝ እንዳለባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረምን አካሂዷል።

በፎረሙም የተለያዩ የውይይት የመነሻ ጥናታዊ ጹህፎች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በፎረሙ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ባለሙያዎች፣ የተለያዩ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ባለሙያዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂኔር ሃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ወቅት የምርምር ተቋማት በውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ በትኩረት በመስራት ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ከተፈጥሮ ጸጋዎቿ እንዳትጠቀም ጫና ሲደረግባት መቆየቱን አንስተው፤ ይህም በልማቷ ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ይህን ጫና በመቀልበስ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያኮራ ተግባር አከናውነዋል ብለዋል።

ለግድቡ ስኬት ርብርብ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ጫና የሚያሳድሩ አካላትን ሃሳብ የማክሸፍ ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

መገናኛ ብዙኃን በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ተግባቦትን በመፍጠር እያከናወኑት ያለውን ተግባርም አድንቀዋል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የመልማት አቋም በማሳወቅ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና መረጋገጥ ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

ለዚሁ ስኬትም የውሃ ተማራማሪና የሚዲያው ዘርፍ ባለሙያዎች ተቀናጅተው በመስራት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህ አኳያ ፎረሙ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶቿን በመጠቀም የምታካሂዳቸውን የልማት ስራዎች ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን በተደራጀ መልኩ ለመመከት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የፍልስፍና እና ማህበራዊ ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ተሾመ አበራ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ  የሚደረገውን ተሳትፎን በማነቃቃት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ተደራሽነት በማሻሻል የኢትዮጵያን የመልማት አቋም በማስቀጠል የዲጂታል ዲፕሎማሲውን ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር ማናየ ዘገየ በበኩላቸው ግብጽ  በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ቋንቋዎች በሚሰሩ በሚዲያዎቿ አማካኝነት በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የጥቅም ፍላጎት ለማሳካት አበክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች መረጃን ተደራሽ ማድረግ የዲፕሎማሲ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በመገንዘብ  ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የአገራቸውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ፤ የኢትዮጵያን እውነትም በተለያዩ ቋንቋዎች በማስረዳት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡