በክልሉ 40 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑ ተመለከተ

129

ሀዋሳ ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት እስከ 40 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል እየተሰራ መሆኑ ተመለከተ ።

የደቡብ ክልል የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት መንደር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ቦኖሾ ጎልቾ ቀበሌ ተካሂዷል።

በፕሮጀክቱ አንድ አርሶ አደር በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ 100 የፍራፍሬ ችግኝ የሚተከል ሲሆን 30 በመቶው በመጀመሪያው ቀሪውን 40 እና 30 በመቶ ደግሞ በ2ኛና በ3ኛ ዓመት የሚተክልበት መርሀ ግብር መሆኑ ተመላክቷል ።

መርሃ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በምክትል ርእሰ መሰተዳድር ማእረግ የክልሉ የገጠር ከላሰተር አሰተባባሪና ግብርና ቢሮ  ኃላፊ አቶ ኡሰማን ሰሩር ናቸው።

አቶ ኡስማን "በመንግሥት የተነደፈው የሶስት ዐመት የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት መንደር ፕሮጀክት የድህነት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው" ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና አላማም በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ በልማቱ በማሳተፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ በተመረጡ የአቮካዶ፤ ሙዝ፤ ፓፓያ እና አፕል ተክሎችን ላይ መሠረት ያደረገ የፍራፍሬ መንደር መመስረትን ያለመ መሆኑንም አክለዋል።

"ልማቱን ማሳካት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው" ያሉት አቶ ኡስማን በተለይ ኢንዲስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ ስራ አጥነት እንዲቀንስና ከቤተሰብ እስከ ሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ክልሉን የማልማት አቅምን መሠረት ያደረገው የፍራፍሬ መንደሮች ምስረታ  ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የልማቱ ተሳታፊዎችን  ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

አንድ አርሶ አደር በሶስት አመት ጊዜ ውሰጥ 100 የተዳቀሉና ምርታማ የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክል እንደሚደረግ ጠቅሰው  የመንግስትና የህብረተሰብ ተቋማት ደግሞ ከ100 እስከ 10 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክሉ እቅድ መያዙን አስረድተዋል።

በፕሮጀክቱ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበርና የመንግስትን ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ህብረተሰቡን ከድህነት ማውጣት ይቻላል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ክፍት መሬት ባላቸው ተቋማት ሁሉ የሚተገበር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው በክልሉ ተመሳሳይ ስነ-ምህዳርን መሠረት በማድረግ 26 የፍራፍሬ መንደርን ለመመስረት ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።

በጥናቱ መሰረት በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ጠቁመው "በአሁኑ ወቅት 400 ሺህ የሙዝ ችግኝ ለ53 ወረዳዎች እየተሰራጨ ነው" ብለዋል።

በሶስት ዓመት ውሰጥም ከ30 እስከ 40 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኝ በማሰራጨትና በማልማት በክልሉ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ልማቱን በትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማትም ተግባራዊ ለማድረግ  በተማሪዎችና በምእመኑ  የችግኝ አቅርቦትና ተከላ እንደሚፈጸም አስረድተዋል።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው ማህበራዊ ተቋማት ተልእኳቸውን ከመወጣት ማሻገር በድህነት ቅነሳ ላይ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ሉቦሶ ዞኑ ያለውን አማራጭ በመጠቀም በሙዝ የበለጸገ አካባቢ ለመፍጠር እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የሻሾጎ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ተማም ከድር እና ተስፋዬ ኤርሴዶ በሰጡት አስተያየት የቤተሰባቸውን አቅም በመጠቀም ባላቸው መሬት ላይ ፍራፍሬን በስፋት ለማልማት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በስነ ስርአቱ ላይ ከክልሉና ከዞኑ የተውጣጡ ከፍተኛ የስሪ ሃላፊዎችና አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም