ህዝብን ለማጋጨት የሚሞክሩ አካላት ላይ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ እንደሚደግፉ ወጣቶች አስታወቁ

74

አርባ ምንጭ፣ ሚያዚያ 28/2014 (ኢዜአ) በሃይማኖት ሽፋን ሀዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ አካላት ላይ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በአርባምንጭ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

ወጣቱን በስሜት ማነሳሳት ወደ ግጭት እንዲያመራ የሚገፋፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ  በቅንጅት  እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ከአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ሱልጣን ሱሌማን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ ሃይማኖትን ተገን በማድረግ ሀገርን ለማፍረስ ህዝቡ አላስፈላጊ ዋጋ እንዲከፍል የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን ተናግሯል፡፡

ይህም ግጭት በመቀስቀስ ለዘመናት የኖረውን የህዝቦች አንድነት ለመናድ በማሴር መሆኑን አውስቷል።

"የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ህዝቡን በማጋጨትና ወጣቱን እንደ መሣሪያ ከሚጠቀሙ አካላት አካባቢያችንን ነቅተን በመጠበቅ ሴራውን ማክሸፍ ይገባናል" ብሏል ወጣት ሱልጣን፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢ ሰሞኑን በተከሰተው ግጭት እጃቸው ያለበትን ግለሰቦች መንግስት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ  እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴም እንደሚደግፍ አስታውቋል።

የሀገርን ሰላም ማረጋገጥ የመንግስት ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ ሁሉም የከተማው ወጣት በመተባበር የድርሻውን እንዲወጣ  እገዛ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

በረመዳን የፆም መልካም ነገሮችን በማሰብና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት የነበረውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል  የተናገረው ደግሞ ወጣት ከድር ሰይድ ነው።

ወጣቱ ስሜታዊ ሆኖ የአፍራሽ አካላት መሳሪያ ከመሆን ይልቅ ለሀገር ሰላምና ልማት አስፈላጊውን በማበርከት የወደፊት ዕድሉን ማሳመር እንዳለበት ጠቁሟል፡፡

ወጣቱ በሰለጠነ መንገድ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በማለፍ የሃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን መልዕክት ማዳመጥ እንደሚገባውም አመልክቷል፡፡

ወጣቱን በስሜት  በማነሳሳት ወደ ግጭት እንዲያመራ የሚገፋፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ   ለማስቻል ከጓደኞቹ ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጿል ፡፡

ወጣት ሰሚራ ኡስማን በበኩሏ፤ በየትኛውም አካባቢ ግጭት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት የትኛውንም ሃይማኖት የሚወክሉ አይደሉም ብላለች፡፡

የሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘመን የማይሽረው አንድነትና አብሮነት ያላቸው መሆኑን ወጣቱ ተገንዝቦ  ከመናናቅ ይልቅ በመከባበር አብሮነቱን ማጠናከር እንዳለበት  አመልክታለች፡፡

ጥፋተኞችን ማለፍ አይገባም ያለችው ወጣቷ፤ በሃይማኖት ሽፋን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚሞክሩ አካላት ላይ መንግስት የሚወስደውን እርምጃ እንደምትደግፍ ገልጻለች።

የህግ የበላይነት እንዲከበር  በምትኖርበት አካባቢ የሚጠበቅባትን እንደምትወጣም ጠቅሳለች፡፡

ወጣቱ በረመዳን የፆም ወቅት የነበረውን መልካም ተግባር በማስቀጠል ለሀገር ሰላም አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፋለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም