መንግሥት ኃይማኖታዊ ግጭት በሚፈጥሩ አካላት ላይ ፈጣንና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ አለበት

107

ሚያዚያ 27 / 2014 (ኢዜአ) መንግሥት ኃይማኖታዊ ግጭት በሚፈጥሩ አካላት ላይ ፈጣንና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤውን አጠናቋል።   

ምክር ቤቱ በጉባኤው በወቅታዊ አገራዊ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ፣ አገራዊ ምክክር፣ የጋራ ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርጅታዊ አቅም፣ የኑሮ ውድነትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቷል።

የጋራ ምክር ቤቱ በተጠቀሱት አጀንዳዎች ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በተቋማዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የአቋም መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት፤ የምክር ቤቱ የሥራ አስፈጻሚ አባልና የፓርቲዎች ጉዳይና ሥልጠና ኃላፊ አላምረው ይርዳው፤ ባለፉት ሳምንታት ኃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ግጭቶች ተከስተዋል ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸው፤ ድርጊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የአብሮነትና የአንድነት እሴት ያፈነገጠ እኩይ ተግባር መሆኑን ነው ያነሱት።

በመሆኑም በኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ግጭቶች እንዳይፈጸሙ መላው ኢትዮጵያዊያንና የሃይማኖት ተቋማት ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጠይቀዋል።

መንግሥት በተለይም የጸጥታ ኃይሉ ኃይማኖታዊ ግጭት በሚፈጥሩ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የፌደራልና የክልል መንግሥታት የማገገሚያ መርኃ-ግብሮች ነድፈው ዜጎቹ ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ምክር ቤቱ አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ካለችበት ዘርፈ-ብዙ ችግር አላቆ የተሻለ ሰላም ለማምጣት ወሳኝ መሆኑን እንደሚያምን ገልጸው፤ የምክር ቤቱ አባላት ፓርቲዎችም ለምክክሩ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።   

በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል መንግሥት ሥር-ነቀል መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎጂ የፖለቲካ ባህሎችን በማስወገድና በምትኩም የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄዳቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ በቀጣዩ ግንቦት ወር የአመራር ምርጫ እንደሚያካሂድም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም