የክልሉ ዕምቅ የቱሪዝም ሀብት የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

147

ሚዛን፣ ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) ..የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ያለው ዕምቅ የቱሪዝም ሀብት ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች እንዲሟሉ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ያለውን ዕምቅ የቱሪዝም ሀብትን ለመጠቀም መሰረተ ልማት ችግርን ለመፍታት ከሚደረገው ጎን ለጎን የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል።

የቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ለኢዜአ እንደገለጹት ክልሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ቢኖሩትም ማልማት ባለመቻሉ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከዘርፉ ማግኘት ሳይቻል ቆይቷል።

በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ስድስቱም ዞኖች ማራኪ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንዳሉ ጠቅሰው ለአብነትም የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ፣ ታሪካዊና ጥንታውያን የእምነት ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ሌሎችም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ዋሻና ሀይቆች እንዲሁም ፏፏቴዎችና አስገራሚ የሆነው የእግዜር ድልድይ የሚባሉት እንደሚገኙ አብራርተዋል።

ኃላፊው ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና የተፈጥሮ መስሂቦች መገኛ ስፍራዎች የመሰረተ ልማት ችግር ያለባቸው በመሆኑ ቱሪስቶችን በመሳብ ሀብት ማመንጨት ላይ ደካማ ነው።

በተለይ የሆቴልና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እጥረት ለመፍታት ቢሮው ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ዘርፉን የሚመጥን መፍትሄ ለማፈላለግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የቱሪስት መስዕብ ቦታዎችን ለሚገበኙ ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ የሆቴል አገልግሎት መፍጠር አንዱ ትኩረት የተሰጠበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚዛን አማን ከተማ ሰሞኑን ተመርቆ ለደምበኞች ከፍት የሆነው በክልሉ የመጀመሪያው በአራት ኮከብ ሳላይሽ ዘግራንድ ሆቴልን  ለአብነት  ጠቅሰዋል።

የሆቴል ኢንቨስትመንት በሁሉም የክልሉ ከተሞች እንዲስፋፋ የክልሉ መንግስት የመሬት አቅርቦትና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አመላክተዋል።

ከዚህም ባሻገር ጎብኚዎች በሚያርፉበት ከተማና ሆቴል አካባቢውን ብሎም ኢትዮጵያን ማወቅ እንዲችሉ የሚያደርጉ ሥራዎች በሆቴል ኢንዱስትሪው ለሚሰሩ ቢሮው ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

"በየዞኑ የሚገኙ የባህል ማዕከላት የሚዘክሩት ታሪክና በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተተገበሩ ያሉ መስዕቦች የቱሪዝም ቀልብ መሳብ የሚችሉ ናቸው" ብለዋል።

የሱርማና መኤን እንዲሁም ሌሎች ብሔረሰቦች የህይወት ዘዬና ባህል የክልሉ ሌላኛው  የቱሪዝም ፀጋዎች መሆናቸውን አውስተዋል።

የመሰረተ ልማት ችግሮች ለመፍታት ከሚደረገው ርብርብ ጎን ለጎን መስዕቦችን በማስተዋወቅ የተለያዩ አስጎበኚ ድርጅቶች ወደ አካባቢው እንዲመጡ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኮይካ በዞኑ ውስጥ በሆቴል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሆቴልና በሌሎች ተመሳሳይ ዘርፎች ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ዝግጁ የሆነ የመሬትና ሌሎች አቅርቦቶች አዘጋጅቶ እየተጠባበቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም በዞኑ ባሉ ከተሞች በተያዘው በጀት ሶስት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ባለኮከብ ሆቴሎች መገንባታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ሆቴሎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው "በዞኑ ውስጥ የሚገኙ የኦሞ ፓርክና የደምቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ለማልማት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ቱሪዝም ብዙ ወጪ ሳይወጣበት ትንሽ ነገር በመጨመርና ሰላምና ፀጥታን ብቻ በመጠበቅ በርካታ የስራ ዕድሎች መፍጠርና ሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት መደገፍ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት የዜጎች ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከርና አካባቢ ልማትና ጥበቃ ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ርብርብ እየተደረገበት መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም