በክልሉ የመኸር እርሻ ግብዓት እጥረትን ለማስተካከል ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ

132

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 27 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለዘንድሮው የመኸር እርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እጥረትን ለማስተካከል ሌሎች አማራጮችን መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ።

የ2014/2015 ክልላዊ የመኸር እርሻ ንቅናቄ መድረክ  በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ  ሃላፊ አቶ ባበክር ከሊፋ በመድረኩ ላይ  እንዳሉት ፤ በክልሉ ለዘንድሮው የመኸር እርሻ ከ100ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን ለማቅረብ ከታቀደው ውስጥ የተገኘው 40 ሺህ ኩንታል ብቻ ነው፡፡

የመኸር ግብርና ግብዓቶችን በጸጥታ ችግር ምክንያት በወቅቱ ለማጓጓዝ ችግር ማጋጠሙን ጠቅሰው፤ ቢሮው ከማዕከል የተፈቀደለትን 40 ሺህ ኩንታል ግብዓት ለማጓጓዝ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ በተለይም የማዳበሪያ ግብዓት እጥረት እንዳያጋጥመው ከወዲሁ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመጠቀም ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በቢሮው የሰብል ልማት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ አቡን በበኩላቸው፤ ባለፈው ዓመት የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው መሬት ለመሰብሰብ ከታቀደው ምርት 51 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ ማሳካት እንደተቻለ አስታውሰዋል፡፡

ምርቱ የተሰበሰበው ከአሶሳ ዞንና ማኦከሞ ልዩ ወረዳ መሆኑን ጠቅሰው፤  በመተከልና ካማሺ ዞኖች የጸጥታ ችግር በማጋጠሙ በግብርና ስራው ላይ እንቅፋት ሆኖ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

የንቅናቄ መድረኩ ባለፈው ዓመት የታጣውን ምርት በዘንድሮው መኸር ለማካካስ በተዘጋጀው እቅድ ግንዛቤ መፍጠርን ታሳቢ ማድረጉንም ተናግረዋል ፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሃብቶች ማህበር ሰብሳቢ አቶ አብዱልማሙድ ኢብራሂም፤   ግብርናውን በማዘመን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር የመንግስት ብቻ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ግብዓቶችን በቁጠባና ሌሎች አማራጮችን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ አመልክተው፤  ማህበሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ የእርሻ ትራክተሮችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ጀምሮ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለማካፈል ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡