የጤና ባለሙያዎች የሀገራችውን ሕልውና ለማስከበር የሰሩት ስራ ሁሌም በታሪክ ሲዘከር ይኖራል- ዶክተር ይልቃል ከፋለ

118

ባህር ዳር ሚያዚያ 27/2014 (ኢዜአ) የጤና ባለሙያዎች የሀገራቸውን ሕልውና ለማስከበር የህይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ለህልውና ዘመቻው ባበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ሁሌም በታሪክ ሲዘከር ይኖራል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

በዘመቻው የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ  ለጤና ባለሙያዎችና ተቋማት የክልሉ ጤና ቢሮ የእውቅና አሰጣጥ መርሃ-ግብር በባህር ዳር ከተማ ዛሬ አካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በመርሃ ግብሩ እንዳሉት የጤና ባለሙያዎች በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው የሀገራቸውን ህልውና ለማስከበር በተደረገው ዘመቻ አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል።

ሀገር ለማፍረስ ታቅዶ የተከፈተን ጦርነት የጤና ባለሙያዎች በተለይ የፀጥታ መዋቅሩ የበለጠ ተጠናክሮ ድል እንዲቀዳጅ ቁሰለኞችን በማከምና በማግልገል ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ገልፀዋል።

በዚህም የፀጥታ መዋቅሩ ተጠናክሮ ለድል እንዲበቃ ካደረጉት ውስጥ የጤና ባለሙያዎች  የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ህዝብ የጤና ባለሙያዎች እስከ ህይወት መስዋትነት የሚጠይቀውን ተጋድሎ በማድረግ ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግ ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አለው ብለዋል።

በህግ ማስከበሩም ሆነ በህልውና ዘመቻው ወቅት የጤና ባለሙያዎች  የቆሰሉ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በማከም የመከላከያ ዩኒቶች መልሰው እንዲጠናከሩ በማድረግ የአንበሳውን ድርሻ መወጣታቸውን የገለጹት ደግሞ የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዥር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ናቸው።

የጤና ባለሙያዎች ዛሬ ላይ የመከላከያ ሠራዊት ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉት የማይተካ አስተዋጽኦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ምስጋናና ክብር አለው ብለዋል።

ጦርነቱ ገና እንዳልተቋጨ ጠቅሰው፤ ጠላት እስካልጠፋ ድረስ ሰላም አይገኝም፤ በቀጣይም ሙያዊ ኃላፊነታችሁን በሚገባ እንደምትወጡ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ  ብለዋል።

”እውቅናው በህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ከልባቸው የሰሩ፣ ያገዙና መስዋዕትነት በመክፈል የታገሉ የጤና ባለሙያዎችን ለማበረታታት ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ናቸው።

በእውቅና መረሃ-ግብሩ ለተሰው የጤና ባለሙያወች ቤተሰቦች፣ ለቆሰሉ የጤና ባለሙያዎችና የአንቡላንስ ሹፌሮች የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን ለተቋማትም የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

በመረሃ-ግብሩ የክልልና የፌደራል፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።