በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል

120

ሚያዚያ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለማቃለል መንግስት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።

በሚኒስትሯ የተመራ ቡድን በክልሉ በድርቁ ምክንያት የቤት እንስሳት አልቀውባቸው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ሴቶችና ህፃናት የሚደረግላቸውን የአስቸኳይ ድርቅ ምላሽ ስራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ሴቶችንና ህጻናት መንግስት ከዩኒሴፍና ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ሚኒስትሯ በወቅቱ እንዳሉት፤ ድርቁ ሴቶችና ህጻናትን ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት አጋልጧል።

የድርቅ አደጋው ዋነኛ ተጎጂ ሴቶች እና ህፃናት መሆናቸውን የተናገሩት ዶክተር ኤርጎጌ፤ እስካሁን በሸበሌ ዞን አዳድሌ ወረዳ ሂግሎ ቀበሌ የተዘጋጀው መጠለያ በሁለት ሚሊዮን ዶላር የምግብ፣ የጤናና የውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል መሰራቱን ጠቁመዋል።

ገንዘቡን የመደበው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህፃናት አድን (ዩኔሴፍ) መሆኑም ተገልጿል።

ነገር ግን የተሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ የሚኒስቴሩ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የፌዴራልና የክልል መንግስታት ለችግር ለተጋለጡ አርብቶ አደር ነዋሪዎች የእለት እርዳታ ለማድረግ የጀመሩት ስራ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሯ ዩኒሴፍ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ከችግሩ ስፋት አኳያ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ ህዝብ ለድርቅ ተጎጂዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የሶማሌ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ አህመድ በሙከራ ደረጃ የተጀመረው ፕሮጀክት 47 ሚሊዮን ብር ከዩኒሴፍ ተመድቦ 10 ሺህ ለሚጠጉ ተጎጂዎች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺህ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በቀጣይም የሀብት ማሰባሰብ ስራ በመስራት በሊባን፣ ቆረሃይ፣ ኖጎብ፣ አፍዴር ዞኖች ተመሳሳይ በድርቅ ለተፈናቃሉ መጠለያ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው የድርቅ ተፈናቃዮች በተሰጣቸው ገንዘብ ልብስና የእለት ምግብ መሸመታቸውን ጠቁመዋል።

የእለት እርዳታው ጊዜያዊ ችግራቸውን ቢያቃልልም በቋሚነት ለመቋቋም እንስሳት እንዲተካላቸው ጠይቀዋል።