ለሠላምና አብሮነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ለማሻገር እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬት ምሁራን ተሳትፋቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

92

ጎባ/ጅማ ሚያዝያ 27/2ዐ14(ኢዜአ) ሠላምና አብሮነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ለማሻገር እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ጥረት ስኬት ምሁራን ተሳትፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ተጠየቀ፡፡

ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲና ከጅማ ዩኒቨርሰቲዎች እንዲሁም ከየዞኖቹ የተውጣጡ ምሁራን የተሳተፉበት የሠላም ኮንፈረንሶች በሮቤ ከተማና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተካሂደዋል።

የሠላም ኮንፈረንሶቹ በሀገሪቱ እየተካሄዱ በሚገኙ የሠላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ የምሁራን ተሳትፎና ምክረ ሀሳብ ለማሳደግ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ተመልክቷል።

በባሌ ሮቤ የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ እንዳሉት፤ ምሁራን ሀገርን በመለወጥና በማሻገር ሂደት ውስጥ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

በምሁራንና በመላው ዜጎች መስዋዕትነት የመጣውን ለውጥ በመቀልበስ ሀገር እንድትፈርስ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች ሴራን ለማክሸፍ ምሁራን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የባሌ ዞን  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዱላ ሂርባዬ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በየምዕራፉ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በመቋቋም ህዝቡን ወደ ብልጽግና ለማሻገር እየሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ በተለይ ምሁራን የዴሞክራሲዊ ሥርዓት በህዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅና ህዝባዊ አንድነትና አብሮነት እንዲጎለብት በማድረግ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከተሳታፊ ምሁራን አቶ አብዱልናሲር አህመድ እንዳሉት መንግሥት ምሁራን ለሀገር እድገትና ብልፅግና ያላቸውን አስተዋኦ በመረዳት ሚናቸውን እንዲወጡ መድረክ መፍጠሩ ጥሩ ጅምር ነው።

መንግሥት ሀገሪቱን ለማሻገር በሁሉም መስክ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅና የሚደግፍ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ዩሱፍ ከድር ናቸው፡፡  

በኮንፈረንስ ላይ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከዞንና ከወረዳዎች የተውጣጡ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን በሰላም፣ በሀገራዊ መግባባት፣ በህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም፣ ሀገራዊ ምክክር እና በሌሎች ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የጅማ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ አካባቢያዊ የሰላምና ደህንነትን ጉዳይ አስመልክቶ “ቀጥተኛ የዜጎች ተሳትፎ ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ ከምህራን ጋር መክሯል፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ አባራያ እንደገለጹት ምሁራን ለሀገር ሰላምና ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸውና የለውጥ መሰረትም ስለሆኑ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።

ምሁራን በየጥናት ዘርፋቸው የበኩላቸውን ለማበርከት የሚደጉትን ጥረት በሀገር ግንባታውም በበለጠ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ከተሳታፊ ምሁራን ዶክተር አብዱሰመድ ሁሴን በበኩላቸው ምንም እንኳን “ምሁራን በቻልነው መጠን ለሀገር ግንባታ ሂደቱ የተቻለንን እያደረግን ቢሆንም ከሚጠበቅብን አንጻር የተሳትፎ መጠናችን ውስን ነው” ብለዋል፡፡

ሀገራችን ካለችበት የሰላምና የደህንነት ችግር እንድትወጣ መንግሥት የሰላም አማራጭን ሁሉ እንዲመረምርም ዶክተር አብዱሰመድ አሳስበዋል፡፡

የጂማ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንጅነር ኤፍሬም ዋቅጂራ በበኩላቸው ሀገር የዴሞክራሲ ምጥ ላይ የምትገኝ በመሆኑ ምሁራንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጊዜውን በጽናት መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።