በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ከ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሽቶ በቁጥጥር ዋለ

206

ፍቼ፣ ሚያዝያ 27/2014/ኢዜአ/ ከመተማ ከተማ በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሽቶ በቁጥጥር ስር መዋሉን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኮሙዩኒኬሽን ዲቪዥን ቡድን መሪ ሳጂን መላኩ ቶላ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሽቶው የተያዘው በወረ ጃርሶ ወረዳ በቀሬ ጐሀ ከተማ የፍተሻ ኬላ በተደረገ ጥብቅ ፍተሻ ነው።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 አአ 54427 በሆነ አይሱዙ የጭነት መኪና ሲጓጓዝ የነበረው 28ሺህ 485 ካርቶን ሽቶ የተያዘው ከትናንት በስትያ ከምሽቱ 4፡ዐዐ ሰዓት ላይ ነው ብለዋል።

ሽቶውን ህጋዊ ህጋዊ አስመስሎ የሰሊጥ ምርት ይለፍ ወረቀት በመያዝ በከሰል ውስጥ ደብቆ ለማስተላለፍ ታልሞ እንደነበር ሳጂን መላኩ ተናግረዋል።

ቡድን መሪው እንዳሉት ሽቶው የኬላው ባለሙያዎችና የወረዳው ንግድ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት የመረጃ ልውውጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

ፖሊስ የመኪናውን አሽከርካሪና ሁለት ተጠርጣሪ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራውን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ ሳጂን መላኩ ጠቁመዋል።

ጥፋተኞች በፈጸሙት ወንጀል ድርጊት እንደሚቀጡ ጠቅሰው፤ ለወንጀል ድርጊት ማስፈጸሚያ የዋለ ተሽከርካሪ ለሕዝብና መንግሥት አገልግሎት እንዲውል ህግ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዞኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አልባሳትን የተለያዩ ዕቃዎችን በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገር የማስገባት አዝማሚያ እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ የንግድ ቁጥጥር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በአካባቢው እየሰራ ነው ብለዋል።

የዞኑ ንግድ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ብርትኳን በቀለ በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋለው ሽቶ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ እንዳያገኝ ማድረጉን ገልፀዋል።