ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመች

154

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመች።

የመግባቢያ ሥምምነቱን የውኃና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ኃብታሙ ኢተፋ ከደቡብ ሱዳን የውኃና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ጋር ተፈራርመዋል።

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ካደረገችው ግንባር ቀደም ድጋፍ ባሻገር ለገጠማት በእርስ በርስ ጦርነት የሰላምና መረጋጋት ፈተና እልባት እንዲያገኝ ብርቱ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ሁለቱ የቁርጥ ቀን ወዳጅ አገሮች ከፖለቲካዊ አጋርነት ባለፈ በምጣኔ ኃብት ረገድም ትስስራቸውን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰሩ ይገኛሉ።

እስካሁን ያመነጨችው የኃይል መጠኗ ከ30 ሜጋ ዋት የማይበልጠው ደቡብ ሱዳን እንደ ጎረቤት አገር  ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ፀጋ መካፈል ትሻለች።

በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን እምቅ የነዳጅ ፀጋ ለመጠቀም ፍላጎት አላት።

በዚህም የልዑካን ቡድኑ ደቡብ ሱዳን ሁለቱ አገራት በኃይል ለመተሳሰር ብሎም አገሪቱ ከኢትዮጵያ ኃይል በምትገዛበት ሁኔታ ላይ ከሥምምነት ለመድረስ ትናንትናው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።

በዚህም በዛሬው የኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ መሰረት በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል ሲሆን በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን  በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህም በሥምምነቱ መሰረት የጥናት ሥራዎች በቅድሚያ የሚከውን ሲሆን በቀጣይ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በሁለቱ አገራት መንግሥታት በኩል በማከናውን ከሦስት ዓመት በኋላ ኃይሉን ወደ አገሪቱ ተደራሽ በማድረግ ገቢራዊ ለማድረግ ታቅዷል።

የኃይል ማስተላለፊያ ሥፍራዎች የአዋጭነት ጥናት በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ የመሰረተ ልማት ግንባታው ሥራ ይጀመራል ተብሏል።

ከሥምምነቱ ቀደም ብሎም ዛሬ ረፋድ የደቡብ ሱዳን የልዑካን ቡድን ብሔራዊ የኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከልንና የኮተቤ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ጎብኝቷል።

ሥምምነቱ ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ አገራቱ ለኃይል ሽያጭ ሥምምነቱ ገቢራዊነትና ለመሰረተ ልማት ዝርጋታው ቁርጠኛ መሆናቸውን ሚኒስትሮች አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ለሱዳንና ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ሲሆን ከኬኒያ ጋርም የሽያጭ ሥምምነቱን ፈፅማ በራሷ የሚጠበቀውን የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዋን ፈፅማለች።

በኬኒያ በኩል የሚካሄደው መሰረተ ልማት ግንባታ መጠናቀቅ የኃይል አቅርቦቱ በይፋ እንደሚጀመር ይጠበቃል።