8 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ ነው

82

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ)  በአዲስ አበባ 8 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የጤና መሰረተ-ልማት ዳይሬክተር ኢንጂነር ታደሰ የማነ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት የሕዝቡን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የህክምና ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ደግሞ በስፋት ሊከሰቱ የሚችሉ የድንገተኛና ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ባለ 11 ወለል ሕንጻ ያለው ሁሉን አቀፍ ሆስፒታል ለመገንባት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

ግንባታው በአዲስ አበባ ለቡ አካባቢ በ11 ሺህ ሜትር ስኩዌር ቦታ ተረክቦ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት መደረጉን ነው ያስረዱት።      

ጎን ለጎንም በ550 ሚሊዮን ብር ወጪ ሁሉን አቀፍ ህንጻ የሚገነባ ሲሆን በውስጡ የህክምና መስጫ ማዕከላት፣ ላቦራቶሪዎችና የምርምር ማዕከላት እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የደም ናሙና ምርመራና የሲቲስካን የመሳሰሉ ውስብስብ ምርመራዎች የሚካሄዱበት ትልቅ የምርመራ ማዕከል በ800 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።  

በአዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚገነባው ለዚሁ የጤና ማዕከል ዲዛይን ተዘጋጅቶ፣ የጨረታው ሂደትም ተጠናቆ ግንባታ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።  

በተጓዳኝም ከቆዳና ቆዳ ነክ ችግሮች ጋር ያለውን ሰፊ የጤና ችግር በዘመናዊ መንገድ ሊያቃልል የሚችል የህክምና ማዕከል ግንባታ በቅርብ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በአለርት ሆስፒታል ለሚገነባው ይኸው ሆስፒታል መንግሥት 2 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸው፤ የግንባታው ዲዛይን ዝግጅት ተጠናቆ ጨረታውም በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።   

ከእነዚህ ግንባታዎች በተጨማሪ ከዓለም ባንክ ከተገኘ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የሁለት ህክምና ተቋማት ግንባታ ሥራ መጀመሩንም አብራርተዋል።

አንደኛው በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ይሆናል የተባለ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ማዕከል መሆኑን ጠቁመው፤  የጨረታ ሂደቱ እየተጠናቀቀ መሆኑንም አስረድተዋል።

በበጀት እጥረት ሥራው ቆሞ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክትም ከባንኩ በተገኘ 1 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ግንባታውን የማስቀጠል ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በማስፋፊያ ግንባታው ደረጃቸውን የጠበቁ የመድኃኒት ማከማቻና ማቀዝቀዣ መጋዘኖች የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎችና በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ሊያስተናግድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።

ሁሉንም ፕሮጀክቶች በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ኢንጂነር ታደሰ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም