ወጣቱ ሰላምን በመጠበቅ የሀገሪቱን ሁለገብ የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ

106

ነቀምቴ፤ ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ)ወጣቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም የአከባቢያውን ሰላም በመጠበቅ የሀገሪቱን ሁለገብ የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።

"የዜጎች ሁለገብ ብልጽግና ተሳትፎ አቅጣጫ" መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በነቀምቴ ተካሂዷል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ወጣቶች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ  አወሉ አብዲ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገሪቱን ሁለገብ የብልጽግና ጉዞን የማረጋገጥ ትልቁ ድርሻ የወጣቱ ነው።

ወጣቱ ከመንግሥት ጎን በመቆም  የአከባቢያውን ሰላም በመጠበቅ  ለሀገር ልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ግንባታና ለሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የአካባቢን ሰላምና ጸጥታ መጠበቅ፣ ነዋሪውን ለልማት ማንቀሳቀስና በሰፊው ደግሞ ለሀገር ደህንነት መከበር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በንቃት በመሳተፍም እንዲሁ።

ወጣቱ የጠላት ተልዕኮ አራማጅ መሆን የለበትም ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ በመደመር ፍልስፍና በመታነጽ በፍቅር፣ በመቻቻል፣ በመደጋገፍና በመደማመጥ በሁሉም ዘርፍ አዲስ ሀሳብን በማፍለቅ ለሀገር ግንባታ ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች የነቀምቴ ከተማ  ነዋሪ  ወጣት ፈቀደ ፍቃዱ በሰጠው አስተያየት፤ በሀገሪቱ በለውጡ አመራር በርካታ መሻሻሉ  መመዝገባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለውጡን ማስቀጠል እንዳለበት ተናግሯል።

ሀገሪቱ  የገጠማትን ችግር ለማቃለል ከመንግሥት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላምና ልማት  የድርሻውን ለመወጣት  ዝግጁ መሆኑን የተናገረው ደግሞ የሐሮ ሊሙ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ዓለሙ አበበ ነው።  

በተለይም በወረዳቸው ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ መንግሥት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ በግንባር ቀደምትነት እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

የሌቃ ዱለቻ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጫላ ዋቅጅራ በበኩሉ፤  ከመንግሥት ጎን በመሆን የአካባቢውን ብሎም የሀገሪቱን  ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማደረግ   ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

 በተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ያለውን የተበላሸ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማስተካከል መንግስት  የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አመልክቷል፡፡

የሀገሪቱን  ሁለገብ ብልጽግና  ለማረጋገጥ  መንግስትን በመደገፍ  የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉም ወጣቶቹ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም