በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ቀን ታስቦ ዋለ

86

ሚያዚያ 27/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አዘጋጅነት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ቀን ታስቦ ውሏል።

ዓለም አቀፍ ደረጃ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ቀን ለ24ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።

ቀኑ የሚከበረው በእሳት አደጋ መከላከል ሂደት ህይወታቸውን ያጡ ሠራተኞችን ለማሰብና ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሐ እንደሚሉት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ በተሰበሰበ መረጃ 11 የኮሚሽኑ ሠራተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ከዚህም ባለፈ በርካታ የኮሚሽኑ ሠራተኞች በአደጋ መከላከል ሂደት ለአካል ጉዳት ጭምር መዳረጋቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የእሳት አደጋ መቆጣጠር ቀን ሲታሰብ እነዚህ ሠራተኞች ለከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ ለመስጠትም መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ሰለሞን አያይዘውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ የእሳት አደጋ የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህ ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሰው በድንገት ከሚከሰቱ አደጋዎች በተጨማሪ የኅብረተሰቡ የጥንቃቄ ጉድለት መሆኑን ገልጸዋል።

ከቴክኖሎጂ መዘመን ጋር ተያይዞም ሰዎች የተለያዩ የኤሌክትሪክ የመገልገያ ዕቃዎችን እየተጠቀሙ በመሆኑ ከጥንቃቄ ጉድለት ጋር የሚያያዙ ናቸው ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከጥንቃቄ ጉድለት እየተበራከተ የመጣውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ በመከላከል ዙሪያ ግንዛቤ  እንደሚሰጥም ገልጸዋል አቶ ሰለሞን።

በኮሚሽኑ ለ34 ዓመታት የእሳት አደጋ ተከላካይነት ያገለገሉት አቶ ጸጋዬ ካሳ እንዳሉት፤ በከተማዋ የአደጋ መከላከል ሂደት በርካታ ተግዳሮቶች አሉ ይላሉ።

ለአብነትም ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ሲደርሱ አንዳንድ ሰዎች መንገዶችን ከመልቀቅ ጀምሮ አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ አለመሆኑን ገልጸዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ ፈጣን እና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እንደሆነም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የ939 የአደጋ መጠቆሚያ ጥሪ መስመር መሆኑ ይታወቃል።

የዓለም አቀፉ የእሳት አደጋ ተከላካይ ቀን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል።