ወጣቱ በኃይማኖት ሽፋን በሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

128

ሚያዚያ 27/2014 (ኢዜአ)  ወጣቱ በኃይማኖት ሽፋን በሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ አባት አርበኞች ጥሪ አቀረቡ።

81ኛው የአርበኞች የድል በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የድል ኃውልት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ተገኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው አባት አርበኞች እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያን ሠላም የማይፈልጉ አካላት በኃይማኖት ሽፋን እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ነው።   

ኢትዮጵዊያን በኃይማኖት ሳይለያዩ ችግሮችን በጋራ ማለፋቸውን ገልጸው አሁንም ይሄ የመጣውን ችግር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መቆም ከቻለ እናልፈዋለን ብለዋል።    

የኃይማኖት ጽንፈኝነትና አክራሪነት ኢትዮጵያዊያንን እንደማይገልጽ ጠቁመው ወጣቱ በኃይማኖት ሽፋን በሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳይጠለፍ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ነው ያሉት።

ከአስተያየት ሰዎቹ መካከል ሻምበል ዋኘው ዓባይ እንደተናገሩት፤ የሁሉም ኃይማኖት ኢትዮጵያዊያን ደማቸውንና አጥንታቸውን ከስክሰው አገር አቆይተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር ሠላማዊና የተረጋጋ አገር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህ የወጣቱ ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን በጦርነትና በኃይል ማሸነፍ ያቃታቸው ኃይሎች በኃይማኖት ሊከፋፍሉን ቆርጠዋል ያሉት ሻምበል ዋኘው ይህንንም ኢትዮጵያዊያን እየተረዱት ነው ብለዋል።

በተለይም ወጣቱ ትውልድ አገር የማቆየት ኃላፊነቱን በአግባቡ ለማስኬድ የጥፋት አጀንዳ ባነገቡ አካላት እንዳይጠለፍ ነገሮችን በጥንቃቄና በስክነት ሊያይ እንደሚገባ አመልክተዋል።   

"ባልሰለጠነው ዘመን በኃይማኖት ተከባብረን ኖረን አሁን በሰለጠነው ዘመን በኃይማኖት የምንናቆርበት ምክንያት አይኖርም" ሲሉም አክለዋል።

የቀድሞ የሰራዊት አባል ባሻ ዳምጠው በበኩላቸው ወጣቶች የቀደሙ አባቶች ህይወት በመማር አሁን የመገጥሙ ፈተናዎችን ለማለፍ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም