በኢትዮጵያ 21 ሚሊዮን የሚሆኑት ሰዎች ሙሉ በሙሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ወስደዋል

119

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት 21 ሚሊዮን የሚሆኑት ሰዎች ሙሉ በሙሉ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መውሰዳቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2ኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት ዘመቻ እና የዘጠኝ ወር የመደበኛ ክትባት አፈጻጸም ግምገማ እያደረገ ነው።

በሚኒስቴሩ የአገልግሎትና ፕሮግራም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አማካሪ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንዳሉት፡ ባለፈው አንድ አመት ከ24 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት ተሰጥቷል።

ከነዚህ ውስጥ 21 ሚሊዮን የሚሆኑት ክትባቱን ሙሉ ለሙሉ የወሰዱ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ ሁለቴ መውሰድ እያለባቸው አንዱን ብቻ የወሰዱ ናቸው።

ክትባቱ በስፋት በመሠጠቱ ወረርሽኙ በአንጻራዊነት እንዲቀንስ ማድረጉን ተናግረዋል።

ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ደርሷል ማለት ባለመሆኑ ህብረተሰቡ መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል።

ሕዝቡ አሁንም በአገሪቱ የክትባት እጥረት እንደሌለ አውቆ ክትባቱን እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።