ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሩጫ ውድድር በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሄደ

ደብረ ማርቆስ፤ ሚያዚያ 27/2014 (ኢዜአ) ''የተፈናቀሉ ወገኖቸን ለመደገፍ እሮጣለሁ'' በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ የሩጫ ውድድር ዛሬ በበምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሄደ።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ቢሻው ሞላ እንደገለጹት፤ ስፖርት አንድነትንና ወንድማማችነትን ማጠናከሪያ መርህን የያዘ ነው።

ዛሬ የተደረገው የሩጫ ውድድር  ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ በማሰባሰብ የህዝቡ አንድነት ጠንካራ  መሆኑን በተግባር ለማሳየት ዓላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሩጫ ውድድሩ ላይ ከ4 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችና በክልሉ ከሚገኙ በአትሌቲክስ ፕሮጀክቶች የታቀፉ አትሌቶች ተሳትፈዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ የሚውለውን የገቢ ማሰባሰቢያ ውድድር የምስራቅ ዞን  ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ፣ የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲና የደብረማርቆስ ስፖርት ፌዴሬሽን በመተባበር እንዳዘጋጁት ተገልጿል።

በተደረገው የሩጫ ከቲሸርት ሽያጭና ከባለሀብቶች ከ229 ሺህ ብር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን በቀጣይም መሰል ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ተመልክቷል።

ከአዊ ልማት ማህበር ቲሊሊ ወረዳ የመጣው አትሌት የኔው ጠብቀው በሰጠው አስተያየት፤ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማገዝ ታስቦ በተዘጋጀው ሩጫ ላይ በመሳተፍ  የድርሻውን መወጣት በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

ቀጣይም ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ዝግጅቶች ሲኖሩ ተሳትፎ በማድረግ የዜግነት ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለተፈናቀሉ ወገኖች ደጋፍ የሚሆን ቲ-ሸርት በ200 ብር በመግዛት በሩጫው ተሳታፊ መሆኑን የተናገሩት  ደግሞ  የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ንጉስ እንዳወቅ ናቸው።

ሩጫ ትልቅ ዓላማ ያነገበ በመሆኑ በቀጣይም በሌሎች ከተሞች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም