ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 37 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኘ

108

አዲስ አበባ ሚያዝያ 27/2014 ኢዜአ/ ባለፉት በዘጠኝ ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 37 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበውን የኤሌክትሪክ ኃይል በማሳደግ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህን ያለው በደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ናስር የተመራ ልዑክ የኢትዮጵያን "ብሔራዊ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል" በጎበኘበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ፕላኒንግ ስራ አስፈፃሚው አቶ አንዷለም ሲያ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የተሻለ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለደቡብ ሱዳን ልዑኩ ማሳዬት መቻሏን ገልጸዋል።

ጉብኝቱም ሁለቱ ሀገራት በሀይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም በመጀመሪያ ምዕራፍ እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለደቡብ ሱዳን 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ያቀደች ሲሆን በሂድት ደግሞ ከ400 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ለማቅረብ ይሰራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ 254 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳንና ጁቡቲ እያቀረበች መሆኗንም ጠቅሰዋል።

ለጎረቤት ሀገራት ከሚቀርብ ኃይል ሽያጭ በዓመት እስከ 50 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ለጎረቤት ሀገራቱ ከቀረበ የኃይል ሽያጭ 37 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው ያስታወቁት።

የደቡብ ሱዳን የኢነርጂና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ በበኩላቸው ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢኮኖሚ እድገት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

ይህን ታሳቢ በማድረግም ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላትን ስምምነት እንዲዳረስ ልዑካቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የስራ ጉብኝት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳድር ነቢል መሓዲ፤ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ግዥ ስምምነት እንድትወስድ የተለያዩ ስራዎች ሲካሄዱ መቆየቱን ገልጸዋል።

የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነት ለማሳዳግም በኃይል፣ በመንገድና ሌሎች የንግድ እንቅስቃሴዎች ለማስታሳሰር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያካሄዱት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ረቂቅ ሰነድ ላይ ምክክር በማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ለታንዛንያ፣ ለሩንዳና ብሩንዲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኃይል መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በትኩረት እየሰራች እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም