የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ሰላምና ነፃነት አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት አለበት -ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

160

ሚያዝያ 27/2014 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ ጀግኖች አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት ሰላምና ነፃነቷ ተጠብቆ የቆየችውን አገር ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ኃላፊነት እንዳለበት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

81ኛው የአርበኞች የድል በዓል መታሰቢያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን  ጨምሮ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሀውልት ተከብሯል።  

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ የበቀል በትር ለማሳረፍ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የፋሺስት ወራሪ ኃይል በጀግኖች አርበኞች መስዋዕትነት መሸነፉን አስታውሰዋል።  

ወራሪውን ኃይል ለማቆም በርካታ አባቶችና እናቶች ተሰውተዋል፤ንብረትም ወድሟል ያሉት ፕሬዝዳንቷ የአርበኞች ጽኑ መስዋዕትነትና ህብረት ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።  

ኢትዮጵያዊያን ያስመዘገቡት አኩሪ ድል በጨለማ ውስጥ ብርሃን መፈለግን የሚያስተምር መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ አኳያ በወቅቱ የነበረው ህብረትና አንድነት አሁን ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍቻነት ሊውል ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።    

በተለይ በጦርነት ምክንያት ለችግር የተጋለጡና ድጋፍ የሚሹ ወጎኖችን መደገፍ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡    

"ሰላም የሰፈነባትን አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ፤ ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በውይይት መፍታትና በሀሳብ የበላይነት ማመን ይገባል ብለዋል።  

በመከላከያ ሚኒስቴር የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል እንዳለ ወልደኪዳን በበኩላቸው አርበኝነት ትውልድ የሚማርበት ኢትዮጵያዊ እሴት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

  

የጀግኖች አርበኞች ታሪክና ተጋድሎ በኢትዮጵያ በየዘመኑ ለሚነሱ ጀግኖች ጠባቂዎች ሞራል የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመከላከያ ሰራዊቱም ከአርበኞች በወረሰው የአይበገሬነት የጠላቶችን አንገት እያስደፋ መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ እንደ ቀድሞ እናትና አባቶቹ ሁሉ ደሙን አፍሶ አጥንቱን ከስክሶ አገር የማስቀጠል ሂደቱን አጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።   

በተለይ ህዝቡን በማሳተፍ አገሪቷ የገጠማትን ችግሮች እንድታልፍ ተግቶ እየሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።  

የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ጀግኖች አርበኞች ዘመናዊ ጦር መስሪያ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል መክተው አገር አቆይተዋል ብለዋል።  

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ አገርን ለማቆየት የተከፈለውን መስዋዕትነት በመገንዘብ የኢትዮጵያ ልማት አርበኛ ሊሆን እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዜጎች ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለኢትዮጵያ ሰላም ዘብ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

አባት አርበኛ ስዩም ኪዳኔ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አርበኞች ዘርና ሃይማኖትን ሳይለዩ አንድ ሆነው መዋደቃቸው ለውጤት አብቅቷቸዋል ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ የእነሱን አርአያና ፈለግ በመከተል አንድነቱን አጠናክሮ አገሩን መጠበቅ አለበት ነው ያሉት፡፡

የአርበኞች የድል በዓል በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን የሚከበር ሲሆን፤ በዓሉ የሚከበረውም  ከዛሬ 81 ዓመት በፊት ጀግኖች አርበኞች በዱር በገደል ተዋድቀው ፋሽስት ጣልያንን በማሸነፍ የኢትዮጵያን ድል ያበሠሩበት እለትን ምክንያት በማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም