የጤና ባለሙያዎች መከላከያ ሰራዊቱ በሁለት እግሩ እንዲቆም የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል - ጄኔራል አበባው ታደሰ

ሚያዚያ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''የጤና ባለሙያዎች የአገር መከላከያ ሰራዊት በሁለት እግሩ እንዲቆም የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል'' ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎችና ተቋማት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር በባህርዳር ከተማ ተካሄዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ “በዘመቻው ወቅት የነበረውን ጉዳት ከጤና ባለሙያው በላይ የሚረዳ የለም” ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ በጦርነቱ የተጎዱ የሰራዊት አባላትን በማከምና በማገልገል ሙያዊና አገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ለሙያቸው ታማኝ ሆነው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አድናቆትና ክብር እንዳለው ተናግረዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በማከም እንደገና ዩኒቶች መልሰው እንዲጠናከሩ በማድረግ የጤና ባለሙያዎቹ ድርሻ የጎላ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ዛሬ መከላከያ ሰራዊት ባለበት ቁመና ላይ እንዲገኝ የጤና ባለሙያዎች የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ በቀጣይ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎቹ ከመከላከያ ሰራዊቱ ባልተናነሰ እስከ ሕይወት መስዋትነት በመክፈል ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።

በአማራ ክልል የጤና ቢሮ አስተባባሪነት ለጤና ባለሙያዎቹ እውቅናው መሰጠቱ ተገልጿል።

መጋቢት 10 ቀን 2014 ዓ.ም በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ለተሳተፉ የህክምና ባለሙያዎች የእውቅና መርሐ ግብር በተከናወነበት ወቅት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የህክምና ባለሙያዎች ግንባር ድረስ በመሄድ ጀግኖቻቸውን በማከም ኢትዮጵያን አድነዋል” ማለታቸው ይታወሳል።

በዛሬው የእውቅና መርሃ ግብር ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም