አሸባሪው ህወሓት የሚፈፅምብን ግፍ ከቀዬአችን አፈናቅሎናል - የትግራይ ክልል ነዋሪዎች

197

ደሴ፣ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት የሚፈፅምብን ግፍና መከራ ከቀዬአችን አፈናቅሎናል ሲሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሃይቅ ጃሬ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን የአማራ ክልል ህዝብ በሚችለው ሁሉ ወገናዊ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ አመልክተዋል።

"ከቄዬአችን ተፈናቅለን ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጥተናል፣ ህዝቡም ተቀብሎ እያስተናገደን ነው” ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የአማራን ህዝብ ጠላት አድርጎ ጥላቻ ቢሰብክም ህዝቡ በፍቅር ተቀብሎ እያስተናገዳቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠላታቸው የአማራ ህዝብ ሳይሆን ለስልጣን ጥሙ ግፍና መከራ የሚፈጽምባቸው ህወሃት እንደሆነም ገልጸዋል።

ቡድኑ ከስምንት ወራት በላይ አስሮ ያሰቃያቸው ከመቀሌ ከተማ የተፈናቀሉት አቶ ጌትነት ስመኘው ለኢዜአ እንደገለፁት፤ አሸባሪው ህወሓት እታገልለታለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ ያተረፈው መከራና ስቃይ ነው።

ቡድኑ ህዝቡን ገንዘብ አምጣ፣ እህል አዋጣና የሚዋጋ ልጅ ስጥ እያለ የሚያሰቃይ መሆኑን ገልጸው፤ የቡድኑን ፍላጎት ማሟላት ያልቻለ ለእስርና ለእንግልት ብሎም ለሞት እንደሚዳረግ ተናግረዋል።

ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በብዙ መከራ አማራ ክልል በመግባታቸው በመንግሥትና በህብረተሰቡ ድጋፍ የዕለት ደራሽ ምግብ፣ አልባሳትና የተለያየ ቁሳቁስ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከአሸባሪው ቡድን ጭቆና ነጻ መውጣታቸው እፎይታ እንደሰጣቸውም ተናግረዋል።

ከመሆኒ ከተማ የተፈናቀለው ወጣት ጀማል መሐመድ እንዳለው የትግራይ ህዝብ የአሸባሪውን ህወሓት ስውር ደባ ተገንዝቦ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በመሆን የሽብር ቡድኑን ማጥፋት አለበት።

''ቡድን ለህዝቡ የሚመጣውን የእርዳታ እህል ለትግራይ ልዩ ኃይልና ለአመራሩ ቤተሰብ ከመስጠቱ በላይ ህዝቡን ሀገር የማፍረስ ሴራውን ለማስፈፀም ገንዝብና ቁሳቁስ እምጡ እያለ መቆሚያና መቀመጫ አሳጥቶታል'' ሲል ተናግሯል።

ወጣት ጀማል አሸባሪው ቡድን ለጦርነት ሊማግደው እንደነበር ገልጾ፤ አልዘምትም በማለቱ ለእስር መዳረጉንና አምስት ሺህ ብር ቅጣት መክፈሉን አንስቷል።

May be an image of 1 person, standing and outdoors

አሸባሪው ህወሓት የሚለውና የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳብ ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን የትግራይ ህዝብ ተገንዝቦ የሽብር ቡድኑን በቃህ ብሎት በጋራ አምርሮ መታገል እንዳለበትም አስገንዝቧል።

የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ የሴቶችን ህይወት አመሰቃቅሏል፤ ወላድ እናቶችን ያለ ልጅ አስቀርቷል፣ ንብረታችንን ዘርፏል ያሉት ደግሞ ከአላማጣ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ፈንታነሽ ኃይሉ ናቸው፡፡

ከቀዬአቸው ተፈናቅለው አማራ ክልል በመግባታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ እርስ በርሳችን የተጋባንና የተዋለድን የማንለያይ ህዝቦች በመሆናችን በደስታ ተቀብለው በማስተናገድ እንደማንለያይ በተግባር አሳይተውናል፡፡

የሽብር ቡድኑ እንዲጠፋና በኢትዮጵያ አስተማማኝ ዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲመጣ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር በበኩላቸው ወደ አማራ ክልል የሚገቡ የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የተጠለሉ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በደቡብ ወሎም ሐይቅ ጃሬ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ከ640 በላይ የትግራይ ተፈናቃይ ወገኖች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

የአማራና የትግራይ ህዝብም ላይለያይ በብዙ ነገሮች የተሳሰረ በመሆኑ ተቀብሎ እየተንከባከባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ህብረተሰቡን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ እያቀረበ ሲሆን ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ አለመሆኑን በተፈናቃዮች ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልፀዋል።

የሁላችንም ጠላት አሸባሪው ህወሓትና ግብረ አብሮቹ በመሆናቸው ቡድኑ ከነክፉ ሃሳቡ እንዲወገድ በጋራ መታገል ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም