የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የድንበር ጉዳዮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብስባ በናይሮቢ ተጀመረ

100

ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የድንበር ጉዳዮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብስባ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ዛሬ ተጀምሯል።

ሁለቱ አገራት ድንበርን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ስራዎች አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በስብስባው ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድንበር ጉዳዮች አማካሪ አቶ ውሂብ ሙሉነህ የተመራ ልዑካን ቡድን እንዲሁም በኬንያ በኩል በኬንያ ፕሬዝዳንት ቢሮ የዓለም አቀፍ ድንበሮች ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ጆን ሙጌንዲ የሚመራ ቡድን እየተሳተፉ እንደሚገኝ አመልክቷል።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ ዓለም ኢትዮጵያና ኬንያ መከባበር፣መተባባርና ዘላቄታዊነት ላይ የተመሰረተ የባለብዙ መስክ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች የፖለቲካ ቁርጠኝነትና በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ያለው የቀረበ ወዳጅነት የሁለትዮሽ ግንኙነቱ መገለጫ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የድንበር ጉዳዮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባዎች የአገራቱን ለረጅም ጊዜ የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ጉርብትና ይበልጥ እንዳጎለበተው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ ድንበራቸውን ለማስጠበቅ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ተፈጻሚነት አስፈላጊውን የፋይናንስ፣የቴክኒክና ሎጅስቲክስ ድጋፎችን እንዲያደርጉ አምባሳደር መለስ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የቴክኒክ ኮሚቴ ስብስባ በኢትዮጵያና ኬንያ የድንበር ማስጠበቅና ቁጥጥር ስራዎች፣የድንበር የጸጥታ ሁኔታ፣የድንበር አካባቢውን በዘመናዊ የመረጃ ስርዓት የማስደገፍ እንዲሁም የበጀትና የስራ እቅድ አስመልክቶ የተዘጋጀውን የ2019 የሞምባሳ ሪፖርት እንደሚገመግም ተገልጿል።

በተጨማሪም የኬንያና ታንዛንያ የድንበር ማስጠበቅ ስራና ቁጥጥር ተሞክሮ በስብሰባው ላይ እንደሚቀርብ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮ-ኬንያ የጋራ የድንበር ጉዳዮች የቴክኒክ ኮሚቴ ስብስባ ከእ.አ.አ 2012 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

ሁለቱ አገራት ከቴክኒክ ኮሚቴ ስብስባ በተጨማሪ የጋራ የሚኒስትሮችና የድንበር ኮሚሽኖችን አቋቁመው በድንበርና በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ዙሪያ በየጊዜው ውይይት ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ እና ኬንያ ድንበር እ.አ.አ 1950 እስከ 1955 መካለሉ የሚታወስ ሲሆን፤የተካለለው ድንበር እ.አ.አ በ1970 ሁለቱ አገራት በፈረሙት የድንበር ስምምነት ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ነው።