የሹዋል ኢድን በዓል ሁሉም በአብሮነት እና በጋራ እንዲያከብር ጥሪ ቀረበ

152

ሐረር፤ ሚያዚያ 26/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በቀጣይ ሳምንት የሚጠበቀው የሹዋል ኢድን በዓል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአብሮነትና በጋራ እንዲያከብሩት የሐረሪ ጉባኤ አፈ -ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ጥሪ አቀረቡ። 

አፈ ጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች በዓሉን የጋራ በማድረግ ወደ ክልሉ በመምጣት አብረን እናክብር ብለዋል ፡፡

በዓሉን ተከትሎ በርካታ እንግዶች ወደ ክልሉ እንደሚመጡ የሚጠበቅ መሆኑን አፈ ጉባኤው ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ በእንግዳ ተቀባይነት እሴቱ ይታወቃል ያሉት  አፈጉባኤው፤ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥንታዊቷ የሐረር ከተማ የሚመጡ እንግዶችን  የክልሉ ህዝብ በሚታወቅበት እንግዳ ተቀባይነት እሴት  ተቀብሎ ሊያስተናገግድ ይገባል ነው ያሉት ፡፡

ሐረር የጥንታዊ የስልጣኔ መገለጫ እንደመሆኑዋ ከአጎራባች ክልሎች እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የቆየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንደነበራትም ጠቅሰዋል፡፡

በዓሉ  በርካታ እንግዶች በሚገኙበት  መከበሩ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ  የህዝብ ለህዝብ ትስስር ይበልጥ ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው ብለዋል ፡፡

የሐረሪ ክልል ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው፤  በዓሉ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሳይበረዙ እሴታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ከማድረግ ባሻገር ህዝቦች እርሰ በእርስ እንዲተዋወቁ እና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲሰፍን የላቀ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያ  ብሄር ብሄረሰቦች በሚገኙበት መከበሩ ቀጠናዊ  ትስስርን ከማስፈን አንጻር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል አቶ ተወለዳ አብዶሽ፡፡

በቀጣይ ሳምንት በሚከበረው የሸዋልኢድ በዓል ላይ    የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ከውጭ   የመጡ እንግዶች  እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።