ለድሬዳዋ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እንሰራለን ነዋሪዎች

99

ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 26/2014 /ኢዜአ/በከተማው ሰላምንና ልማትን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት በማገዝ ሀላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

በድሬዳዋ ከተማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

መንግስት ኃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ሰላምንና ልማትን በሚያውኩ አካላት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊዎች አመልክተዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ በድሪያ ኢብራሂም  እንዳሉት "የሚፈለገው ብልጽግና  እንዲረጋገጥና የአገሪቱን ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላምን በተቀናጀ መንገድ ማስፈን ይገባል" ብለዋል።

"ነዋሪዎች ከመንግስት ጎን በመቆም ብሔርና ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱ አካላትን ለህግ ማቅረብ አለብን" ብለዋል፡፡

 ህዝብን በተለይ ወጣቱ ለሰላምና ለልማት ብቻ እንዲተጋ  ወላጆች ኃላፊነት  ወስደው  መንቀሳቀስ እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ ማህደረ አብራሃም ናቸው፡፡

 "ህዝብና የጸጥታ አካላት በመቀናጀት  ዜጎች ህገ- መንግስቱ ያረጋገጠላቸውን ሰርቶ የማግኘትና በነጻነት በመረጡት አካባቢ የመኖር መብትን የሚያውኩ  አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ  ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል፡፡

በከተማው በተለያዩ አዳራሾች የተካሄዱ ውይይቶችን የመሩት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች መንግስት በዜጎች መካከል ጥላቻና መቃቃርን በመፍጠር ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ አንግበው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ነዋሪዎች  መንግስት የጥፋት አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለህግ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ሀላፊዎቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም