ቢሮው ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ

104

ሰቆጣ ፤ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህውሓት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ደረገ።


የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ ለኢዜአ እንደገለፁት የሽብር ቡድኑ በፈፀመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ኅብረተሰቡንና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበር የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

ሀላፊዋ እንዳሉት የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለማቃለል ድጋፉ የተደረገው ለ50 ያህል አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችና ለሚያጠቡ እናቶች ነው።

ድጋፉ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሩዝ፣ በርበሬና የማብሰያ ቁሳቁሶች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ እንደሚያካትትም ገልፀዋል።


እንዲሁም በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች መሰረታዊ ችግሮቻቸውን በመለየት ለመንግሥትና ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች በማቅረብ እንዲፈቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።


የተፈናቃይ ወገኖችን መሰረታዊ ችግር ለመፍታትም ባለሃብቶች፣ በጎ ፈቃደኞች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም ማህበረሰቡ በሚችለው አቅም ሁሉ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


የዞኑ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሪት ካባ ሲሳይ እንዳሉት በዞኑ በአሸባሪው ህውሓት ወረራ ከ86 ሺህ በላይ ወገኖች ተፈናቅለው በሰቆጣ፣ ወለህና ፅፅቃ መጠለያ ጣብያዎች ይገኛሉ።


በቢሮው በኩል የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍም አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ያሉባቸውን ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እንዲረባረቡም አሳስበዋል።

ቢሮው ቀደም ሲል በሽብር ቡድኑ ወረራ በዞኑ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖችም 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም