ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የጥፋት ድርጊት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 145 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ-አስተዳደሩ

226

አዳማ፣ ሚያዝያ 26/2014/ኢዜአ/ በጎንደር የተከሰተውን ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ የጥፋት ድርጊት ለመድገም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 145 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዳማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተኮረ ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት የግል የፖለቲካ ጥቅማቸውን ማዕከል በማድረግ በሀይማኖት ሽፋን ሀገራዊ ትርምስ ለመፍጠር እየሰሩ ያሉ አካላትን  ስራ ማክሸፍ ከወጣቱ የሚጠበቅ ቀዳሚ ተግባር ነው።

በጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች የተከሰተውን ሀይማኖትን ሽፋን ያደረገ እኩይ ተግባር አዳማ ለማምጣት ብዙ ጥረቶች መደረጋቸውን የጠቀሱት ከንቲባው በጉዳዩ ዙሪያ ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት አባቶች ጋር ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።

ድርጊቱን ከማውገዝ ባሻገር ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ስርዓት ማስያዝ መቻሉን ተናግረዋል።

ፅንፈኛ ሃይሎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በጎንደር የፈፀሙትን የጥፋት ድርጊት ለማስፋትና ትርምስ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 145 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ዘጠኝ የሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው ህዝቡን በብልሹ አሰራርና  ሌብነት ያስመረሩ 69 አመራሮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ከንቲባው ተናግረዋል።

የመድረኩ ዓላማ ወጣቶች የፅንፈኞችን የጥፋት ተልዕኮ ተረድተው የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲጫወቱ  ለማስቻል መሆኑን ገልፀዋል።

በየደረጃው ያለው የወጣቶች አደረጃጀት በነቃ መንፈስ የአፍራሽ ሃይሎችን ሴራ በማጋለጥ የአካባቢያቸውንና የከተማዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲጠብቁ ማስቻል ሌላው የመድረኩ አላማ መሆኑን አመልክተዋል።

በጽንፈኞችና በአክራሪዎች ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በማጋለጥና በማክሸፍ በከተማዋም ሆነ በክልሉ ቦታ እንዳይኖራቸው ለማስቻል መድረኩ አስተዋጾ ያለው መሆኑን አስታውቀዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ ከተሳተፉት ወጣቶች መካከል “ራሄል ከበደ የሀገራችን አንድነት ለማስቀጠል የሃይማኖቶችም ሆነ የብሔሮችን እኩልነት አምነን መቀበል አለብን” ብላለች።

የሚያዋጣን አንድነታችን ነው፣ ኦሮሞ፣ አማራና ሌላውም ብሔር አንዱ ከአንዱ አይበላለጥም  ያለችው ወጣቷ “ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም እንደ በፊቱ ተከባብረን መኖር ነው የሚያዋጣን” ብላለች።

“ፖለቲካውን ፖለቲከኞች ይስሩት፤ እኛ እንደ ወጣት የአካባቢያችንን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ላይ መረባረብ አለብን፤ የሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ዓላማ ተሸካሚ መሆን የለብንም” ስትል አክላለች።

ሌላው ተሳታፊ ወጣት ደፋሩ መንግስቱ በበኩሉ “የጥፋት ድርጊት የሚፈፅሙ የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎች በመሆናቸው ወጣቱ ይህንን ተረድቶ ሴራቸውን ለማክሸፍ እየሰራ ይገኛል” ብሏል።

“ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሀገርና የህዝቦቿን ሰላም የሚነሱ አካላት ላይ መንግስት የማያደግም አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፤ እኛም የድርሻችንን እንወጣለን” ብሏል።

“ህብረተሰቡ የሚጠብቀው መንግስት ተገቢውን የማስተማሪያ እርምጃ እንዲወስድ ነው” ያለው ወጣቱ፣ “እኛም በወጣቶች አደረጃጀት በኩል ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም እየጠበቅን ነው” ብሏል።