በልማት ድርጅቶች ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነትና የሥራ ቦታ ትብብርን ለማስፈን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

95

ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ልማት ድርጅቶች ከድርጅቶቹ የሰራተኛ ማህበራት ተወካዮች ጋር የሥራ ቦታ ትብብርና የማህበራዊ ምክክር ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ የተፈረመው በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አመቻችነት መሆኑም ታውቋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አሰግድ ጌታቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስምምነቱ በድርጅቶች ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲመሰረትና ትብብርን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው።

ስምምነቱ ሰራተኛውም ሆነ አሰሪው ግዴታቸውን አክብረውና ተረድተው በመግባባትና በመተባበር ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፉ ይረዳልም ብለዋል፡፡

በሥራ አካባቢ ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር በቀጣሪ ድርጅቶችና ሰራተኞች መካከል የሚያጋጥሙ ችግሮችን በድርድር ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት፡፡

ሚኒስቴሩ የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ተግባር መግባቱን የገለጹት አቶ አሰግድ፤ ይህን እቅድ ለማሳካት ደግሞ አሰሪና ሰራተኞች ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ ብለዋል፡፡

ድርጅቶቹና የሰራተኛ ማህበራቱ በልማት ሥራው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አቅማቸውን የመገንባት ሥራ በተከታታይነት ይሰራልም ነው ያሉት።

በመሆኑም እነዚህ ወገኖች በሚሰሩበት አካባቢ መብቶቻቸውና ግዴታቸውን አውቀው ጤናማ የሥራ ግንኙነት መስርተው የሚሰሩበት ጉዳይ ትኩረት እንደሚሰጠውም አክለዋል፡፡

የአሰሪውንም ሆነ የሰራተኛውን ጥቅም ይበልጥ ለማስጠበቅ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ተሻሽሎ መውጣቱን በዋናነት ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ የሁለቱንም ወገኖች መብትና ግዴታ ወሰን በግልጽ ያስቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የልማት ተቋማቱና የሰራተኛ ማህበራቱ ተወካዮች በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ሰራተኛው ሥራው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርግ ድርጅቱ ደግሞ ምርታማ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል፡፡

ይህ የሥራ ቦታ ትብብርና ማህበራዊ ምክክር የሰራተኛውንና የአሰሪውን ጥቅም በማስጠበቅ፣ የሥራ ላይ ጤንነትንና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

ስምምነቱ አለመግባባቶችና ቅሬታዎች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ሳይሄዱ በውይይትና በድርድር እንዲፈቱም ያግዛል ብለዋል፡፡

በሰራተኛው በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በፍጥነት ምላሽ ለመስጠትና  የመረጃ ልውውጥን ለማሳለጥም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡