በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር በማካሄድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን--የአውሮፓ ህብረት

95

ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር በማካሄድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ቢሮ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በየዓመቱ ግንቦት 9 የሚከበረውን ''የአውሮፓ ቀን" አስመልክቶ ዛሬ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ቀኑ 72 ዓመታት ያስቆጠረውን የአውሮፓ ህብረት ምስረታ ታሳቢ በማድረግ የሚከበር መሆኑ ይታወቃል፡፡

በመርሃ ግብሩም ህብረቱ ከኢትዮጵያና አፍሪካ ህብረት ጋር ያለውን ትብብር የሚዳስሱ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ በዚሁ ወቅት፤ ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በዚህም ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በሰላምና ጸጥታ፣ በንግድ፣በትምህርትና ሌሎች ዘርፎች በትብብር እየሰራ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡

የአውሮፓ ህብረትና ኢትዮጵያ ጠንካራ የንግድ ልውውጥ አጋርነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ወጪ ንግድ መካከል 20 በመቶ የሚሆነው ወደ አውሮፓ ህብረት አባል አገራት እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት መደበኛ ሳይሆን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት እንዳላቸውም ነው አምባሳደር ሮላንድ ኮቢያ ያብራሩት፡፡

ይህም ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ህብረቱ ከተመሰረተባቸው ዓብይ ዓላማዎች መካከል ሰላምን ማረጋገጥ አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ህብረቱ  ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶችን ያበረታታል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር  በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት፡፡

በአፍሪካ ህብረት የአውሮፓ ህብረት ጉዳይ አስፈጻሚ ፓትሪክ ዱፖንት በበኩላቸው የአውሮፓ ህብረት፣ በአፍሪካ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍንና የተረጋጋ የፖለቲካ ሂደት እንዲኖር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረቱ በተለይ በአህጉሪቱ በኢኮኖሚ መስክና በተለያዩ ዘርፎች ትስስር እንዲኖር እየደገፈ ስለመሆኑም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም