በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን ድርቁን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው መዘገባቸው ተገለጸ

185

ጅግጅጋ፣ ሚያዚያ 26/2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሱ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙሃን በክልሉ ድርቅ መከሰቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ ተከታትለው በመዘገብ በሁሉም አካላት ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጋቸውን የክልሉ ጋዜጠኞች ማህበር አስታወቀ።

ዓለም አቀፍ የሚዲያ ነፃነት ቀን “ጋዜጠኝነት በዲጄታል ዘመን” በሚል መሪ ሃሳብ ማህበሩ ባዘጋጀው  ፓናል ውይይት በጅግጅጋ ከተማ ትናንት ታስቦ ውሏል።

የማህበሩ ሊቀመንበር ወይዝሮ አያን ሹክሪ በዚሁ ጊዜ እንደገለጸችው ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን በክልሉ ሲከበር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በክልሉ 15 የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍተው እየሰሩ መሆናቸውን አስረድታለች።

መገናኛ ብዙሃን ድርቁ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥትን  ጨምሮ  በተለያዩ  አካላት  የተደረጉ ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ዋነኛ አጃንዳቸው አደርገው  መዘገባቸውን  ተናግራለች።

ሊቀመንበሯ እንዳለችው በዚህም ድርቅ ባጋጠመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲያገኙና ኅብረተሰቡ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህል እንዲያጎለብት ውጤታማ ስራ ሰርቷል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው “የነፃነትና የእኩልነት” ሀገር አቀፍ ተፎካካሪ ፓርቲ ቃል አቀባይ አቶ አብዲላሂ አብዲኑር በበኩላቸው የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ  ህግ መንግሥታዊ ዋስትና ማግኘቱን ተናግረዋል።

አክለውም “ከአራት ዓመታት በፊት በክልሉ እንኳን የግል ሚዲያ ማቋቋም ቀርቶ፤ በነፃነት ሀሳብን በተለያየ መንገድ መግለጽ ይፈራ ነበረ” ብለዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ በተከፈቱ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከመፈጠሩም ባሻገር፤ የሀሳብ ማንሸራሸርያና ለትውልድ የዕውቀት ማስተላለፊያ ማዕከላት መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ጋዜጠኞች ማህበር ባለፈው ዓመት የተቋቋመ ሲሆን፤ 70 አባላት እንዳሉትም ተመልክቷል።