በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪና ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል

125

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸመውን ስርቆት ለመከላከል ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪና ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳሰቡ።

ሁለቱ ተቋማት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ስርቆትና ውድመት በመጠንና በስፋት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው ስርቆቱ የጨመረው ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።  

በመሆኑም የሚመለከተው አካል ወንጀለኞች ላይ አስተማሪና ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ ይህንን ትልቅ የሕዝብ ኃብት መከላከል እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ እንደገለጹት፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያ እየተከናወነ ነው።

በዚህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ የተደረገባቸው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውንና ይህም የተቋሙን አገልግሎት ከማስተጓጎል ባሻገር ደንበኞችን ለእንግልት መዳረጉን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ተቋሙ ክስ ቢመሰርትም ወንጀል በመከላከልና አስተማሪ ቅጣት በማስተላለፍ በኩል ውስንነቶች እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ስርቆት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በመጠንም በስፋትም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚፈጸሙት ወንጀሎች ለመጨመር ምክንያትም በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪና ተመጣጣኝ አለመሆኑን ነው ያነሱት።   

የፍትህ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አወል ሱልጣን በበኩላቸው፤ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚሰጡ መሳሪያዎች ላይ የሚፈጸሙ ስርቆቶች በከባድ ወንጀል ያስጠይቃሉ ብለዋል።

ወንጀሉን ለመከላከል የወጣን አዋጅ ተከትሎ ተቋሙ ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ ክስ መስርቶ ቅጣት እንዲጣልባቸው በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው ያስረዱት።

እንዲያም ሆኖ ድርጊቱን የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን በሚፈለገው ደረጃ ለሕግ የማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው፤ ይህንንም ለማስተካከል የመፍትሔ እርምጃዎች  እንደሚወሰዱ ገልጸዋል።  

ሁለቱ ተቋማት በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ የሚደረግ ውድመት የአገርን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚገታና ተጠቃሚው ኅብረተሰብን የሚጎዳ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተዘረጋውንና 20ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የኤሌክትሪክ መስመር የጸጥታ ኃይሉ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ጥበቃ ሊያደርግለት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም