የአህሪ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መሥጠት ይጀምራል

109

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት /አህሪ/ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የመሰረተ ልማት ዳይሬክተር ኢንጂነር ታደሰ የማነ እንደገለጹት፤ የአገሪቱን የሕክምና አሰጣጥ አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን እየተካሄዱ ነው።

ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ አለርት ሆስፒታል ውስጥ የሚገነባው አጠቃላይ የድንገተኛ አደጋዎች ሆስፒታል አንዱ መሆኑን ጠቁመው ግንባታው 43 መድረሱን ተናግረዋል።

ግንባታው ከሁለት ዓመታት በፊት እንደተጀመረና በ750 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተካሄደ መሆን ጠቅሰው ወጪውን ሙሉ በሙሉ የሸፈነው መንግሥት መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታው በስምንት ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን 11 ወለሎች እንዳሉት ጠቅሰዋል።  

ሆስፒታሉ አምስት መቶ መኝታ ክፍሎችና 16 የኦፕራሲይን ክፍሎችን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ያካተተ ነው ብለዋል።  

ግንባታው ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት መጨረሻ አከባቢ አገልግሎት መሥጠት እንደሚችል ጠቁመዋል።

ሌላው በአለርት ሆስፒታል ውስጥ በግንባታ ላይ ያለው የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት /አህሪ/ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል ግንባታ 93 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በውስጡ 72 ደረጃቸውን የጠበቁ ላብራቶሪዎችና 68 የምርምር ክፍሎች ይዟል ብለዋል።

ከ550 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው ይኸው ማዕከል በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ላይ ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ተቋማት ከኢትዮጵያ አልፎ በተለይም ለአፍሪካ አገራት ሕሙማንና ተመራማሪዎችም አገልግሎት መስጠት በሚችል መልኩ መገንባታቸው ተገልጿል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም