ህብረተሰቡ በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ አካላት እንዲጠበቅ እያስተማርኩ ነው – ጉባዔው

168

ሶዶ ፤ ሚያዝያ 25/2014 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የጥፋት አጀንዳ ይዘው በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ አካላት በመጠበቅ ለአካባቢው ሰላም መከበር የድርሻውን እንዲወጣ እያስተማረ መሆኑን የወላይታ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ።

በአንዳንዳ የሀገሪቱ አካባቢ ሰሞኑን  እምነትን ተገን በማድረግ በተፈጠረው ችግር ማዘኑን በመግለጽ ድርጊቱን አውግዟል።

ጉባኤው እንዳመለከተው፤  ህብረተሰቡ  በእምነት ሽፋን ጽንፈኞች እየፈጠሩት ያለውን ችግር እንዲከላከሉ ለማስቻል በቅንጅት እየሰራ ነው።

ድብቅ አጀንዳ ይዘው በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ አካላት የእምነት ተከታዮች ተጠብቀው የአካባቢያቸውን ሰላም እንዲስከብሩ እያስተማረ መሆኑን ገልጿል።

የጉባኤው አስተባባሪ አቶ ሚልኪያስ ኦሎሎ በሰጡት ማብራሪያ ፤ በእምነት ስም የሚንቀሳቀሱት ቡድኖች እየፈጠሩት ያለውን ችግር  ምዕመናን በአግባቡ ተረድተው  የተሳሳተውን ለመመለስ የድርሻቸውን  እንዲወጡ ጥረት እየተደረገ ነው ።

ለዚህም በጉባዔው ስራ የሚገኙ   የእምነት ተቋማት ለተከታዮቻቸው በተቀናጀ መንገድ ትምህርት በመስጠት  ጽንፈኞችን  እንዲከላከሉ እየተሰራ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶችና ባህሎች ያሏቸው ህዝቦች ተዋደውና ተቻችለው በመኖር ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን ያስታወሱት አስተባባሪው፤  ጠላትን በጋራ  በመመከት ዳር ድንበራቸውን አስከብረው በኖሩበት ሀገር በሀይማኖት ሽፋን  ግጭት ማስነሳት ፈር የለቀቀ ተግባር መሆኑን አመላክተዋል።

የጉባዔው አባልና የዞኑ የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሐጂ ናስር የሱፍ በበኩላቸው፤ ሃይማኖት ለመጠበቅ በሚል ሀሳብ ሀይማኖት የማይፈቅደውን ተግባር መፈፀም ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

”አንድነታችንን ሊያደፈርሱ ለሚፈልጉ አካላት ዕድል  መስጠት የለብንም” ብለዋል።

ወጣቱ በፅንፈኞች ግፊት  ለስህተት እንዳይጋለጥ  በቤተ እምነት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሀይማኖት ተግባራት በቀዳሚነት ሰላምና ሰብአዊነት ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለዚህ ተገዥ የማይሆን ራሱን መፈተሽ እንደሚገባውና ራሱን የማያይ ትውልድ ካጋጠመ ወላጆችና ቤተሰቦች በመገሰጽ  ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል።

የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት በስማ በለው ብቻ ይዞ ጥላቻ ከማሰራጨት የድርጊቱን መንስኤ በመረዳት ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አነሰተዋል።

”ሃይማኖቶች በስነምግባር የታነፁ ዜጎች ማፍሪያ ተቋማት እንጂ  የፀጥታ ስጋት ሊሆን አይገባም” ያሉት ደግሞ ሌላው የጉባኤው አባል መላከ ፀሐይ ቀሲስ አለማየሁ አማረ ናቸው።

ምዕመናን በሃይማኖት ሽፋን  የጥፋት  ዓላማ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላትን ጠንቅቀው ማወቅና መከላከል፤ የሃይማኖት መሪዎችም ማስተማር ይጠበቅብናል ብለዋል።