የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ሁለቱ ኮሚሽኖች ያካሄዷቸው ጥናቶችና ያገኟቸው ተሞክሮዎች ለአገራዊ ምክክሩ በግብዓትነት እንዲውሉ ይሰራል

153

ሚያዝያ 25/2014 (ኢዜአ)  የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት የእርቀ ሰላም ኮሚሽንና የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ያካሄዷቸውን ጥናቶችና ያገኟቸው ተሞክሮዎች ለአገራዊ ምክክሩ በግብዓትነት እንዲያገለግሉ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገለጸ።

የኅዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሥራ ዘመናቸው ላጠናቀቁት የእርቀ ሰላም ኮሚሽንና የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን እውቅና ሰጥተዋል።

የኮሚሽኖቹን የሥራ ዘመን ቆይታ በሚመለከትም ውይይትም ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ የሁለቱም ኮሚሽን ሰብሳቢዎች እስካሁን የነበራቸውን የሥራ ሂደት የሚዳስስ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን አገራዊ የምክክር ኮሚሽንም እንዲሁ በቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ ያከናወናቸውን ተግባራትና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን አቅርቧል።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል ኮሚሽኑ 41 አባላትን ይዞ መቋቋሙን አንስተው ኮሚሽኑ ሥራ ከመግባቱ በፊት ለአገራዊ እርቁ ጠቃሚ የሆኑ አገር በቀል እውቀቶችን የማጥናት ሂደት ማካሄዱን ገልጸዋል።

ለዚህም ኅብረተሰቡን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማወያየታቸውን ጠቁመው በአገሪቱ በተለያዩ  አካባቢዎች መደማመጥና መሰማማትን እንዲሁም መከባበርን መሰረት ያደረጉ በርካታ የእርቅ ሥርዓት መኖራቸውን መገንዘብ ተችሏል ብለዋል።

ጎን ለጎንም ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በጥንቃቄ መቀመራቸውን ገልጸው የእርቅ ሂደቱን ለማስጀመር የሚያስችሉ ሠነዶች ተዘጋጅተው እንደነበረ አንስተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ይህንን ሠነድ መነሻ በማድረግ ወደ ማስታረቁና ማስማማቱ ሂደት የመግባት ሥራዎች ሲጀመሩ የኮሚሽኑ የሥራ ግዜ መጠናቀቁን ገልጸው ሠነዱን  ወደ ሥራ ማስገባት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በቀጣይም የኮሚሽኑ አባላት በቅርቡ የተቋቋመው አገራዊ ኮሚሽኑ ግቡን እንዲመታ በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።   

የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሰብሳቢ ዶክተር ጣሰው ገብሬ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ምንም እንኳን በ41 አባላት ሥራ ቢጀምርም ተልዕኮውን ለመወጣት ተጨማሪ አደረጃጀቶችን መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ከኮሚሽኑ ከማንነትና ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ምክረ ኃሳቦችን ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ አገር አቀፍ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ ኮሚሽኑ በጥናቱ መሰረት አሰፈላጊውን ምክረ ኃሳብ ለማቅረብ እየተንደረደረ ባለበት ጊዜ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመኑ ማብቃቱን ገልጸው ጥናቱ ተግባራዊ እንዲሆን ጠይቀዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው የሥራ ዘመናቸውን ያጠናቀቁት ሁለቱም ኮሚሽኖች አባላት እውነተኛ አገር ወዳድ መሆናቸውን ገልጸው አርአያነትን በተላበሰ መልኩ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ቸረዋቸዋል።

በተለይም ያለምንም የፋይናንስና የግብዓት ድጋፍ የህዝብንና የመንግሥትን አደራ ለመወጣት በባለቤትነት መሥራታቸው ለዚህች አገር መቀጠል ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ያሳያልም ብለዋል።

አገራዊ የምክከር ኮሚሽኑ ከሁለቱ ኮሚሽኖች የተረከበውን የጥናትና የምርምር ውጤቶችን ጨምሮ ጠቃሚ ግብዓቶችን ሕጋዊ አካሄዶች በጠበቀ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑ እንደሚሰራ ገልጸዋል።   

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር እንዲሁ ሁለቱም ኮሚሽኖች የተቋቋሙበት ወቅትና ጊዜ እጅግ አስፈላጊና ትክክለኛ ውሳኔ እንደነበር ጠቁመዋል።

ኮሚሽኖቹ ሲቋቋሙ የሕግ ክፍተቶች ጨምሮ ሌሎች ክፍተቶችን እንደነበሩባቸው ተናግረው እነዚህም ችግሮች ኮሚሽኑ በሚጠበቀው ደረጃ ስኬታማ እንዳይሆኑ ማድረጉን ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች በመለየትና በማረም እንዲሁም የተሻሉ ልምዶችን በመቀመር ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ምክር ቤቱ በቁርጠኝነት ይሰራል ነው ያሉት።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው፤ ከኮሚሽኑ ከተለያዩ አካላት የሚገኙ ግብዓቶችና መልካም ተሞክሮዎችን ለመቀመር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሁለቱ ኮሚሽኖች የተወሰዱ መልካም ተሞክሮዎችን እንዲሁም የማስተካከያ እርምቶችን በመተግበር በጋራ ስኬታማ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።