የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የፊታችን ሐሙስ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

163

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምስራቅ አፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የፊታችን ሐሙስ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡

ፌዴሬሽኑ የውድድሩን ዝግጅት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ፤ ውድድሩ ከሚያዚያ 27 እስከ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውድድሩን የምታዘጋጀው ከ28 ዓመት በኋላ መሆኑን ጠቅሰው፤  ውድድሩን  የአገርን ገጽታ ለመገንባት በሚስያችል መልኩ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁንም ነው የተናገሩት።

ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን ከታቻለ በቀጣይ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድሮች ለማዘጋጀት እድል እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።

እስካሁን ባለው ሂደት በወድድሩ ስድስት አገራት እንደሚሳተፉ የታወቀ ሲሆን፤ ቀሪ ተሳታፊ አገራትም ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የውድድሩ ተሳታፊ አገራት በወንድና በሴት እስከ  አምስት አትሌቶች የማሳተፍ እድል ያላቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የውድድሩ አዘጋጅ በመሆኗ ተጨማሪ አትሌቶችን የማሳተፍ እድል አግኝታለች፡፡

በዚህም 10 ወንድና 10 ሴት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

የስፖርት ቤተሰቡ በውድድሩ ቦታ በመገኘት ኢትዮጵያዊን አትሌቶችን እንዲያበረታታ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ብዛኔ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የውድድሩ መክፍቻ ሐሙስ ጠዋት 3፡00 ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚካሄድ ይሆናል።