የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በዘላቂነት ለማልማትና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ ነው-ሚኒስቴሩ

112

ሚዛን አማን፣ ሚያዝያ 25/2014 (ኢዜአ)የኢንዱስትሪ ዘርፉ ን በዘላቂነት ለማልማትና ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ “ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገራዊ ንቅናቄን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ በንቅናቄ መድረኩ  ላይ እንደገለጹት በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ጉልህ ድርሻ አለው።

ለሽግግሩእውን መሆን ለኢንዱስትሪዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በስፋት ማምረትና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች መፍታት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

“ኢትዮጵያ ታምርት” ሀገር አቀፍ ንቅናቄ  ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን  አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል።

“ንቅናቄው ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩ ዘርፉ አስተዋፅኦ ለማበርከት ያስችለዋል” ሲሉ አክለዋል።

በተለይ ዜጎች ለሀገር ውስጥ ምርት ቅድሚያ በመስጠት ለኢንዱስትሪዎች ማበብና መስፋፋት የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአገር ውስጥ ምርትን በኩራት ለመጠቀም በየደረጃው የሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት በቂ ምርት  እንዲመረት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 ክልሉ ካለው ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት በቅንጅት ከተሰራበት የኢንዱስትሪ ማዕከል የሚሆንበት ሰፊ ዕድል እንዳለው ሚኒስትር ዴኤታው አመልከተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ መሠረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጅዋ ሳፒ በበኩላቸው ክልሉ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

እምቅ የወርቅ፣ የቡና፣ የማርና የድንጋይ ከሰልን ጨምሮ ሌሎችም የተፈጥሮ ሀብቶች በስፋት ቢኖሩትም ፤ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አምርታ እንድትበለጽግ አርሶና አርብቶ አደሩ በዘመናዊ መንገድ ማምረት እንዳለበት ጠቅሰው፡  በቅርቡ የተዋቀረው የክልሉ መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ቤተልሔም ዳንኤል በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ የግብርና ዘርፍ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሆን በቂ ምርት እንዲያመርት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተሳስረው የገቢ ምርትን የሚተካ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ  አሁንያሉትን 1ሺህ 480 ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በ2017 ዓም ወደ 3 ሺህ ለማሳደግ ታቅዷል አስታውቀዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከሚኒስቴሩ፣ ከክልሉና ከዞኖች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።