በሶማሌ ክልል በ372 ሚሊዮን ብር በጀት አጣዳፊ የድርቅ ምላሽ ፕሮጀክት ስራ እየተካሄደ ነው

170

ጂግጅጋ፤ ሚያዚያ 25/2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል በ372 ሚሊዮን ብር በጀት አጣዳፊ የድርቅ ምላሽ ፕሮጀክት ስራ እየተካሄደ መሆኑን በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስታወቀ።


የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙክታር መዓሊን አብዲ  እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ድርቁ ካስከተለባቸው ተፅዕኖ እንዲያገግሙ ከዓለም ባንክ በተመደበ  በጀት ነው እየተካሄደ ያለው።

የግጦሽ መሬትን ማስተዳደር ፣ አርብቶ አደሩ ከድርቅና ከአየር ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም እንዲችል ማገዝ፣የአቅም ግንባታ ሥራዎች፣ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ተቋማት ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል በፕሮጀክቱ  ትኩረት ከሚደረግባቸው መካከል ይገኙበታል።  

አሁን ላይ  አምስት መቶ ሄክታር መሬት በፍጥነት የሚደርስ  የተመጣጠነ የእንስሳት ሳር በጎዴ፣ በዶሎ አዶ፣ አዳድሌና ዶሎ ባይ ወረዳዎች ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመቀናጀት በመስኖ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም አስራ አንድ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ 32 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የማሻሻያና ጥገና  ስራዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

ይህ ስራ የሚካሄደው ከውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር መሆኑን አስረድተዋል።

በጀቱ  በክልሉ ሃምሳ አራት ወረዳዎች የሚገኙ እንስሳትን ድርቁ ካስከተለው ጉዳት ለመታደግ በተለያዩ ተቋማት የተገዙ የእንስሳት መኖ የማጓጓዣ ወጪን እንደሚያካትትም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። 

ለአምስት ዓመታት ለሚዘልቀው ፕሮጀክቱ  ተጨማሪ በጀት እንዳለውና ከሁለት ሚሊየን በላይ አርብቶ አደሮችን እና ከፊል አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ  የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ እስካሁንም  አምስት የእንስሳት ጤና ኬላዎችና አምስት መለስተኛ የእንስሳት ገበያ ማዕከላት ግንባታ ተጠናቋል፤ አንድ መቶ ሀያ ሺህ እስር መኖ ለወረዳዎች ተከፋፍሏል።

የእንስሳት ሀብቱን ለማዘመን የተሻለ የወተት ተዋፅኦና ስጋ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው  1ሺህ 440 ፍየልና በጎችን ለአንድ መቶ አርባ አራት ቡድኖች መከፋፈሉንም አንሰተዋል።

በ216 ማህበራት ለተደራጁ  ሴቶችና ወጣቶች  የስራ ማንቀሳቀሻ   ሠላሳ ሰባት ሚሊየን ብር ተዘዋዋሪ ብድር መሰጠቱንም ጠቅሰዋል።

በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ  የጥናትና ምርምር ስራዎችን ከጂግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም  ከክልሉ እርሻና እንስሳት ምርምር ተቋም ጋር  በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል ።

በዋርዴር  ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በአነስተኛ ንግድ የተሰማራው የአንፈዓ ህብረት ስራ ማህበር አባል ወጣት ቃሊ ሼክ ኢብራሂም በሰጠችው አስተያየት፤ ከፕሮጀክቱ ባገኙት ሶስት መቶ ሺህ ብር በእህል ንግድ ተሰማርተው  የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውን መግለጿን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።