በሃይማኖት ሽፋን እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ድርጊት የትኛውንም እምነት አይወክልም - የሃይማኖት አባቶች

95

ሚያዝያ 25/2014 ነቀምቴ (ኢዜአ) በሃይማኖት ሽፋን እየተፈፀመ ያለው አስነዋሪ ድርጊት የትኛውንም እምነት አይወክልም ሲሉ የነቀምቴ ከተማ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

ከሃይማኖት አባቶቹ መካከል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምሥራቅ ወለጋ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ገነት ቆሞስ አባ ወልደ ገብረኤል እንደገለፁት   ጎንደር ላይ ሰሞኑን በሀይማኖት ሽፋን የተፈጠረው ግጭት ሊከሰት የማይገባውና እጅግ አስነዋሪ  ተግባር ነው፡፡

"ድርጊቱ  አሳዛኝና በየትኛውም መስፈርት ለአገር ትልቅ ኪሳራ ነው" ብለዋል፡፡

"መንግሥት በአገሪቱ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መከላከል ይኖርባታል" ያሉት የሃይማኖት አባቱ "ችግሮች ቢፈጠሩም  ሥር ሣይሰዱ ለጉዳዩ መፍትሔ መስጠት ከመንግሥት ይጠበቃል" በማለት አመልክተዋል፡፡

"አገር የሚባለው ሰው ነው፤ ሰው እየሞተ የሚቀጥል ከሆነ አገር እንደፈረሰ ይታየኛል’’ ያሉት አባ ወልደ ገብርኤል አበበ በጎንደር የተፈጠረው ችግር  መወገዝ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በሀይማኖት መካከል ጣልቃ በመግባት ትርፍ ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ርካሽ አስተሳሰብ አራማጆችን  ለመከላከል የሁሉም ሀይማኖት ተከታዮች መንገዳቸውን መዝጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

መንግሥትም የጉዳዩ ባለቤቶችን ተከታትሎ ለሕግ ማቅረብ  አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት  ዋና ሥራ አስኪያጁ  አስገንዝበዋል ።

የነቀምቴ ፈትህ መስጊድ ኢማም ሼህ መሐመድ አወል ማህመድ በበኩላቸው በጎንደር የተከሰተው ድርጊት በማንኛውም መስፈርት የማይደገፍና ማንኛውንም እምነት የማይወክል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ድርጊቱ ከሀይማኖት አስተምህሮት ውጭ ስለሆነ ሁሉም ራሱን ከመሰል ተግባር መጠበቅ እንዳለበት አመልክተዋል።

"መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ጥፋተኞቹን ለሕግ ማቅረብ ይኖርበታል" ብለዋል።

ከጥንት ጀምሮ የነበረው አንድነት፣ አብሮነት፣ ሕብረት፣ መተባበር፣ መከባበርና መቻቻል በተጠናከረ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

የነቀምቴ ፈትህ መስጊድ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ናስር በበኩላቸው በጎንደር የተደረገው ድርጊት ከሀይማኖት አስተምህሮ ውጭ የተደረገ በመሆኑ እንዳሳዘናቸውና  አጥብቀው እንደሚያወግዙት ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱን "የሁሉንም ሀይማኖት የማይወክል" ሲሉት ገልጸውታል።

 መንግሥት አጥፊዎችን በማጋለጥ ለሕግ ሊያቀርብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም