“በህዳሴው ግድብና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች ከሽፈዋል” – የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

79

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በህዳሴው ግድብና በከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶችን ማክሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለፀ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው፣ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን መልካም ነገር ማየት በማይፈልጉ የውስጥና የውጪ ኃይሎች የሚደገፉ አካላት ህዳሴው ግድብ ላይ በተቀናጀ መልኩ የሳይበር ጦርነት ከፍተው ነበር።

ጥቃቶቹ ምንም ጉዳት ሳያደርሱ እንዲመክኑ ተደርጓል።በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የሳይበር ጥቃቶች በባለሙያዎች ጥረት እንዲከሽፉ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።

የሃገሪቱን ሰላምና ዕድገት በማይፈልጉ ሃገራት የሚደገፍ ድርጅት የህዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በማቀድ ‘ብላክ ፒራሚድ ወር’ በሚል ስያሜ የሳይበር ጦርነት ከፍቷል።

ይሁንና የጥፋት አላማ አቅደው ሲያሴሩ የነበሩት ሁሉ እንዳሰቡት ሕልማቸው ሳይሳካ ተጨናግፏል ብለዋል።ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፤ ከህዳሴው ግድብ ውኃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ብላክ ፒራሚድ ወር የሚባል የኮምፒውተር ቫይረስ ተሠርቶ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ተደርጓል።

በተለይም የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ 37 ሺህ ኮምፒውተሮችን ላይ ጥቃት በመፈጸም የህዳሴው ግድብን ለማስተጓጎል ተሞክሯል።

ጥቃቶቹም በኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር ጥብቅ ክትትል ምንም ጉዳት ሳያደርሱ እንዲቋረጡና እንዲመክኑ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። የህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችል ይገመታል ያሉት ዶክተር ሹመቴ፤ ከዚህ በኋላም የሳይበር ምሕዳሩን በመጠቀም ግድቡ በአግባቡ ኃይል እንዳያመነጭና እንዲቆም ጥረት ሊያደርጉ የሚችል አካላት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

ለዚህም ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተግባራዊ በማድረግ ከህዳሴው ግድብ ግንባታና ቁጥጥር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ ግድቡን በተመለከተ ከአመራረት እስከ ግንባታ ዕቃዎች ማጓጓዣ የሚያጠቃልሉ ሥራዎች ላይ የሳይበር ምህዳሩን በመጠቀም ከፍተኛ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።

በህዳሴው ግድብ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶች እስካሁን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርሱ እንዲመክኑ ቢደረግም አሁንም የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ኢነርጂ ተቋማት ሁሉ ፋይናንስ ተቋማትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የሳይበር ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁልጊዜም አንድ እርምጃ ቀድሞ ማየት፣ ማቀድና መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ሰብረው መግባት ከቻሉ መዘዛቸው ብዙ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የተቃጡት ጥቃቶች ቢሳኩ ኖሮ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በሃገር ደረጃ ከፍተኛ ችግር ያስከትሉ እንደነበር ገልጸዋል።

የፋይናንስ ተቋማትን ከጥቃት ለመከላከል ልዩ ትኩረት እናደርጋለን ያሉት ዶክተር ሹመቴ፤ ይሁንና ተቋማቱም ከነዚህ ዓይነት ጥቃቶች ራሳቸውን ለመጠበቅና ለመከላከል አስፈላጊ የሚባሉ ዝግጅቶችን ማድረግ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

በተለይ የፋይናንስ ተቋማት የሳይበር ደህንነት ላይ የሚመድቧቸው ሰዎች በሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር ምሉዕ መሆን አለባቸው።

በተጨማሪ የተቋማቱን ቴክኖሎጂ በየጊዜው ማዘመንና ኦዲት ማስደረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ ሥራ የአንድ ተቋም ሥራ ብቻ ሊሆን አይችልም ያሉት ዶክተር ሹመቴ፤ ሁሉም አካላት በኃላፊነት መንፈስ በመሥራት ከሳይበር ጥቃት ደህንነታቸው የተጠበቀ ተቋማትን መገንባት አለብን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለአብነትም በኢትዮጵያ ብቻ በ2013 ዓ.ም የደረሰው የሳይበር ጥቃት ሙከራ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መጨመሩንና በ2014 ዓ.ም ግማሽ ዓመት ላይም ከ3400 በላይ ከፍተኛ እና አደገኛ የሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተመከቱ ዶክተር ሹመቴ አንስተዋል።

እንደ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ከሆነ፤ የዲጂታል ሥነ ምህዳሩ ላይ የሚገቡና የሚወጡ ማናቸውም መረጃዎች ጤናማ ስለመሆናቸው ቁጥጥር ይደረግባቸዋል::

የሳይበር ጥቃት የሚመስል መረጃ ከተገኘ የቅድመ መከላከል ዕርምጃ ይወሰዳል። ከዚያ አልፎ የሚመጣ ካለ ደግሞ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ይወሰዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም