ደኖችን በቋሚነት መጠበቅ የአረንጓዴ ልማት ስኬት ማረጋገጫ ነው -ተመራማሪዎች

261

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)የአፍሪካን ደኖች በቋሚነት መጠበቅና ማልማት የአረንጓዴ ልማትን ማረጋገጫ ቁልፍ መንገድ መሆኑን አፍሪካውያን ተመራማሪዎች አመለከቱ።

በደቡብ ኮርያ ሴኡል እየተካሄደ በሚገኘው 15ኛው የደን ልማት ፎረም ላይ የሚሳተፉ አፍሪካውያን የዘርፉ ተመራማሪዎች “የአየር ንብረት ለውጥ፣ ኋላቀር የመሬት አጠቃቀም፣የከተሞች መስፋፋት የአፍሪካን ጥብቅ ደኖች ይዞታ እያመናመነው ይገኛል” ብለዋል።

ይህም በአህጉሩ የአረንጓዴ ልማት ስኬት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል ያሉት ተመራማሪዎቹ የአረንጓዴ ልማት ግቦችን ለማሳካትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የደኖችን ሕልውና መጠበቅ ያስፈልጋል ሲሉ አመልክተዋል።

“ደኖቻችንን በዘላቂነት መጠበቅና ማልማት የአረንጓዴ ልማት ስኬትን በዋናነት የሚወስኑ ጉዳዮች ናቸው” ሲሉ ነው ያመለከቱት ።

ደኖችን በዘላቂነት ለማልማትና ለመጠበቅ የከሰልና የማገዶ አጠቃቀምን በሌሎች አማራጮች ለመተካት የሚያስችሉ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ደኖቹ በዙሪያቸው ላሉ ማህበረሰቦች ኢኮኖሚያዊ ምንጮች እንደመሆናቸው ነዋሪዎቹን ታሳቢ ያደረጉ የልማትና ጥበቃ ስራዎች ማከናነወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

ተመራማሪዎቹ መንግስታት በደኑ ዙርያ ላሉ ማህበረሰቦች የተፈጥሮ ሃብት ሳይጎዳ መገኘት የሚችሉ ምግቦችን፣የሃይል አቅርቦቶትንና ኢኮ ቱሪዝምን ማስተዋወቅ ይገባቸዋል ብለዋል።

የአለማችን 16 በመቶ የሚሆነው የደን ሽፋን በአፍሪካ እንደሚገኝ ባለሙያዎቹን ጠቅሶ ሲጂቲኤን ዘግቧል።