በ10 ዓመቱ የቤት ልማት መሪ ዕቅድ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤቶች ይገነባሉ

291

ሚያዝያ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ10 ዓመቱ የቤት ልማት መሪ ዕቅድ 4 ነጥብ 4 ሚሊየን የከተማ ቤቶች ለመገንባት ማቀዱን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

ከዚህ ባለፈም በገጠር የቤት ልማት ንዑስ ፕሮግራም 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የሚደርሱ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተመላክቷል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ለማሸጋገር በዛሬው ዕለት አገር አቀፍ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በስራ ላይ የነበሩት የከተማ ቤት አቅርቦት የስትራቴጂ ማዕቀፍና የገጠር ቤት ልማት ስትራቴጂን በማሻሻል የግል ሴክተሩን ተሳትፎ ለማሳደግ መሰራቱን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ከተሞች ተደራሽና ተመጣጣኝ የመኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት፣ በጥራትና በብዛት ለማቅረብ ይሰራሌ ነው ያሉት ፡፡

ከዚህ ባለፈ ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ለማጎልበት ብሎም ያረጁና የተፋፈጉ የከተማ አካባቢዎችን ለማደስ አዲሱ ሴትራቴጂ ይግዛል ነው ያሉት፡፡

ካለፉት ዓመታት የልማት ውጤቶችና ልምድ በመነሳት በአገረቱ በመኖሪያ ቤት ልማትና አስተዳደር ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ በማድረግ በቤት ልማት ዘርፍ የግል ሴክተሩ የአንበሳውን ድርሻ እንዲወስድ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

እንደ ኤፍ ቢ ሲ ዘገባ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም በከተሞች ለመገንባታ ከተያዘው 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ቤት ውስጥ የግል ሴክተሩ 80 በመቶውን ይሸፍናል ።

ከእቅዱ ጋር ተያይዞም በመካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የሚያስችሉ አቅሞችና ዕድሎችን በሚገባ በመፈተሽ፣ የአቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

የሪል ስቴት ዘርፉ ተገቢው የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅለት በማድረግ እያደገ የሚሄደውን የቤት ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማስተናገድ ና የሪል ስቴት አልሚዎች በተገቢው መንገድ እንዲደራጁ የመንግስትን ድጋፍ መጠቀም እንዲችሉ እንደሚያግዝም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም