ያዳበርነውን በመቻቻልና በመከባበር አብሮ የመኖር እሴትን ይበልጥ እናጠናክራለን

215

አሶሳ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሌሎች ሃይማኖቶች ተከታዮች ጋር ያዳበሩትን በመቻቻልና በመከባበር አብሮ የመኖር እሴት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአሶሳ የኢድ አል ፈጥር በዓል ላይ የታደሙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ፡፡

በአሶሳ 1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ሲከበር የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ አብዱለጢፍ አልከድር እንዳሉት፤ በቅርቡ በሃገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የጸጥታ ችግር በየትኛውም ሃይማኖት ተቀባይነት የለውም፡፡

''አንዳችን የሌላችንን እምነት ማክበር የግድ ነው'' ያሉት አቶ አብዱለጢፍ፤ ክብር የሚገኘው የሌላውን ስብዕና በመጠበቅና በማክበር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሼህ አብደላ መሐመድ በበኩላቸው እስልምና ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ እንዲከበሩ የሚያዝ ሀይማኖት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''ከማንኛውም ሃይማኖት ጋር ተቻችለን እንድንኖርም ሃይማኖቱ ያዛል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ችግሮች ሲከሰቱ ደግሞ ከስሜታዊነት በመውጣት በሰከነ መንገድ ነገሮችን መመልከት እንደሚገባ መክረዋል።

ጽንፈኞች ሃገርን ለማተራመስ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የተናገሩት የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱልሙኒየም አብዱልዋሂድ፤ በከተማው የእስልምናና ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በጋራ ሆነው ችግረኞችን ከመርዳት ጀምሮ በዓሉን በጋራ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡ የጽንፈኞች መጠቀሚያ ሳይሆን ለሀገሩ ሰላም እንዲቆም ጠይቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሐጂ ከራር አልቀሪብ "ኢትዮጵያ የተደቀኑባትን ፈተናዎች እንድታልፍ ዜጎች በሰከነ መንፈስ ነገሮችን ማጤን ይገባቸዋል" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም