ህዝበ ሙስሊሙ በጾም ወቅት ያሳየውን መደጋገፍና አብሮነት አጠናክሮ መቀጠል አለበት

141

ጋምቤላ፣ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ በፆም ወቅት ያሳየውን መደጋገፍና አብሮነት ከኢድ አል ፈጥር በዓል በኋላም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋምቤላ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አሳሰቡ።

የኢድ አል ፈጥር የሶላት ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ጠዋት በጋምቤላ ከተማ የሃይማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም ተካሄዷል።

የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ሲራጅ አማን በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመደገፍና አብሮነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በተለይም በረመዳን ወቅት ያሳየውን መተሳሰብ፣ መደጋገፍ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም የማይፈልጉ ጽንፈኛ ቡድኖች በሃይማኖቶች ሽፋን ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን አብሮነትና መቻቻል ለማሻከር የሸረቡት ሴራ የትኛውንም እምነት ስለማይወክል ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ።

በሶላት የተሳተፉት ምዕመናን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አባቶች ያቆዩትን ህብረትና አንድነት በማጠናከርና የሌላቸውን መደገፍ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም አባቶች በአብሮነት፣ በመቻቻል ያቆይዋት ሀገር በዚህም ትውልድ ተጠብቃ እንደምትቀጥል እምነታቸውን ተናግረዋል።

የትኛውንም እምነት በማይወክሉ ጥቂት ጽንፈኛ የጥፋት ቡድኖች ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ለማጋጨት የተደረገው ሙከራ የሚወገዝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህን መሰል እኩይ ሴራ ለመፈጸም የሚሞክሩ የተዛባ አመለካከት ያላቸውን ጽንፈኞች ሁሉም የእምነት ተከታይ ሊኮንኗቸውና ችግር ፈጣሪዎችንም ለህግ አሳልፎ መስጠት ይገባል ብለዋል።

በፆሙ ወቅት አቅመ ደካሞችና የሌላቸውን በመደገፍ የታየውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም